የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ ክንውን ሪፖርት ዕቅድ ሚያዝያ 7/2016 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል ቀርቦ ተገምግሟል ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲውን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት በመገምገም ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠልና ደካማ አፈፃፀም የታየባቸው መስኮችን በመለየት በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠር የግምገማ መድረኩ ዓላማ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልጸዋል፡፡

የስትራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ሰለሞን ይፍሩ ባቀረቡት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እና በአመራርና አስተዳደር ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ቀርበዋል፡፡

የመማር ማስተማር፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም የማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ሥራዎችን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የመሥራት ደረጃን ለማሻሻል በትኩረት መሥራት፣ የምርምር ሥራ ውጤቶች እና የተላመዱና የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ የማሸጋገር ሥራ አጠናክሮ መሥራት፣ ከኦዲት ግኝት የጸዳ ተቋም ለመሆን በትኩረት መሥራት፣ የገቢ ማመንጫ አማራጮችን በማበራከትና አሠራሮችን በማሻሻል ገቢን ማሳደግ፣ ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና አዲስ የተጀመሩት በብቃት እንዲሠሩ ትኩረት ሰጥቶ መደገፍ፣ የቅድመ ምረቃ ተመራቂ ተማሪዎች በመውጫ ፈተና የማለፍ መጠን እንዲጨምር የመማር ማስተማር አፈጻጸም ጥራትን ማሻሻል፣ በዩኒቨርሲቲው አዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት ጥናት መሠረት የሠራተኛ ምደባ ሥራን በትኩረት ማከናወን፣ የትምህርት ፕሮግራሞች ክለሳ ሥራን በትኩረት ማከናወን፣ የዩኒቨርሲቲውን ጆርናሎች እና የትምህርት ፕሮግራሞች አክሬዲት ለማድረግ በትኩረት መሥራት፣ የዩኒቨርሲቲውን የማስተማሪያና ሪፌራል ሆስፒታል ሥራ ማስጀመር፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ግራንት ከውጭ የማግኘት ደረጃን ማሳደግ፣ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲሆን የተጀመረውን ጥናት በትኩረት መሥራት እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው በተሰጠው ልየታና ትኩረት መስክ ላይ አጠናክሮ ለመሥራት እየተዘጋጀ ያለውን የውስጥ አሠራር መመሪያ በማጠናቀቅ ተግባራዊ ማድረግ በቀጣይ ጊዜያት ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የተማሪ ምግብ ጥሬ ዕቃን ጨምሮ የግብዓት አቅርቦት የገበያ ዋጋ ንረት፣ የሰርቪስና የመስክ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች ቁጥር ከሥራው ጋር አለመመጣጠን እና ያሉ ተሽከርካሪዎችም ያረጁ ከመሆናቸው አንጻር ከፍተኛ የጥገና ወጪ እየወጣ መሆኑ እንዲሁም በመደበኛ ቅድመ ምረቃ የአዲስ ተማሪዎች ምደባ ዘግይቶ ከመፈጸሙ ጋር ተያይዞ የትምህርት ካላንደርን ከበጀት ዘመን ጋር አጣጥሞ መፈጸም አለመቻል በግማሽ ዓመቱ ከገጠሙ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም ከካውንስሉ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከዘርፍ ከፍተኛ አመራሮችና ከሌሎች የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት