የአርባ ምንጭ የኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ከጀርመን ልማት ኤጀንሲ/GIZ/ ጋር በመተባበር የነፃ ሕግ ድጋፍ አገልግሎት ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂዎች ለማድረስ ያለመ የጋራ ትብብር ፕሮጀክት የማስጀመሪያና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መርሃ ግብሮችን ሚያዝያ 7/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለጹት በሕግ ትምህርት ቤት አማካኝነት በነፃ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት የሚሰጠው አገልግሎት የሰዎችን ሰብአዊ መብት ብሎም የመኖር ያለመኖር ህልውናቸውን ያስከበረ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ፕሮጀክቱም እነዚህን ሥራዎች የበለጠ የሚደግፍ በጀት ይዞ የመጣ ነው እንደ መሆኑ በመደበኛው በጀት መሥራት የማይቻሉ ተግባራትን ከአጋር ድርጅቶች ጋር የመሥራት ልምድን ትምህርት ቤቱ  እንዲያካብት ማስቻሉን ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡ እንደ ሀገር ከፍተኛ ችግር እየሆነ ለመጣው ሕገ ወጥ መፈናቀል መርሃ ግብሩ መፍትሔ የሚሰጥ በመሆኑም ፍልሰትን ለመከላከል በሕግ ዘርፍ የምንሰጠው አገልግሎት የሚቆጠርና የሚታይ እንዲሆን ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡ ዶ/ር ተክሉ በመጨረሻም ከጀርመን ልማት ኤጀንሲ ጋር በቀጣይ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እንደሚሠሩና የሁል ጊዜ አጋራቸው እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የሕግ ትምህርት ቤት ዲን መ/ር ዳኛቸው ወርቁ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ዓላማ ቀድሞ የነበረውን የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ማስፋፋትና ማጠናከር በተለይም በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎች እና ሌሎችም ለጥቃቱ ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦችን መደገፍ መሆኑን አመላክተዋል፡፡  ተጠቃሚዎቹ በዋናነት ለጥቃቱ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰባችን ክፍሎች፡- ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች  እና ታራሚዎችን እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ በራሳቸው ወጪ የጥብቅና አገልግሎት ማግኘት የማይችሉትንም የሚያጠቃልል ሲሆን አገልግሎቱን ለማግኘት ከሚመለከተው የመንግሥት አካል መረጃ ማግኘት ይጠበቃል ብለዋል፡፡  

እንደ ዲኑ ገለጻ በጀርመን ልማት ኤጀንሲ ረገድ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ዘጠኝ መቶ አሥራ አንድ ሺህ አራት መቶ ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን በዚህም ወክሎ በመከራከር ለ60 ሰዎች፣ የሕግ ምክር በመስጠት ለ300፣ በአቤቱታ ዝግጅት ለ700 እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ለ45‚000 ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም በየሴክተሩ ባሉ ማዕከላት ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎችን የሚቀጥርና የቢሮ ዕቃዎችን የሚያሟላ ሲሆን ፍርድ ቤቶችም ፕሮግራሙ በሚተገበርባቸው አካባቢዎች ያሉ የነፃ የሕግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ቢሮዎችን እንደሚያሟሉ መ/ር ዳኛቸው ጠቁመዋል፡፡ የፕሮጀክቱም የቆይታ 98 ቀናት ሲሆን ከመጋቢት 13/2016 ጀምሮ የዳሰሳ ጥናትና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች መሰጠት መጀመራቸውን የገለጹት መ/ር ዳኛቸው በፕሮጀክቱ ትኩረት የሚደረግባቸውና አገልግሎቱን የሚያገኙ አካባቢዎችም በጋሞ ዞን የሚገኙ 6 ወረዳዎች እና 3 ከተማ አስተዳደሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የብሔራዊ ቅብብሎሽ ሥርዓትን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት በፍትህ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከፍተኛ አቃቢ ሕግ ወ/ሮ መቅደስ ፈከነ ባቀረቡት ሰነድ የቅብብሎሽ ሥርዓት ውስጥ ተቋማት የራሳቸውን አገልግሎት የሚሰጡና መሸፈን የማይችሉትን ለሌላ ተቋም የሚልኩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አክለውም የፍትሕ ሚኒስቴር ተጎጂዎች ከምርመራ በፊትና በምርመራ ወቅት የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ሰብዓዊ መብቶቻቸው መረጋገጣቸውንና ቆይታቸው የት እንደሆነ ማረጋገጥ፣ በክርክር ሂደት ምቹ ሁኔታን መፍጠርና ከለላ ማድረግ፣ ጊዜያዊ መጠለያ መስጠት እንዲሁም የሥነ ልቦና ድጋፍ ማድረግና መሰል ተግባራት ለፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ የተሰጠ ሥራ መሆኑን ወ/ሮ መቅደስ ጠቁመዋል፡፡  

ሰዎችን መነገድና በሕገ ወጥ መንገድ ማሻገር በሚል የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው ሕግ ትምህርት ቤት የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር በላይነህ ብርሃኑ በሰዎች መነገድ ወይም ሕገ ወጥ ዝውውር ዓላማው ብዝበዛ ሆኖ  ሰዎችን በዛቻ፣ በኃይል፣ በማገት፣ በተንኮል፣ በማስገደድና ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም ሰዎችን ማጓጓዝና ለተለያየ ዓላማ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር እንዲሁም ማስጠለል መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ተሳታፊዎቹም ተጠቂ ተብለው እንደሚወሰዱና ድርጊቱም በዓለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ድንጋጌዎች ላይ ከኢሰብኣዊ አያያዝ የመጠበቅ አንደኛው መብት መሆኑን ባቀረቡት ሰነድ አመላክተዋል፡፡  በሌላ በኩል ድንበር ማሻገር ዜጋ ያልሆነን ሰው ወደ ሌላ ሀገር ማሻገር ሲሆን ፈጻሚውም ሆነ ተሻጋሪው የገንዘብ እና ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት በስምምነት የሚያደርጉት ተግባር  መሆኑን ዶ/ር በላይነህ አክለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር በላነይነህ በሰዎች መነገድን ለመከላከል በ2000 ዓ/ም በወጣው ፕሮቶኮል በሰዎች መነገድን መከላከልና መቆጣጠር ተጎጂዎችን መጠበቅና ማገዝ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብር መፍጠር ሲሆን በዚህም ረገድ በሀገራት ላይ የተጣለውም ግዴታ ድርጊቱን ወንጀል ማድረግ፣ ጥበቃ ማድረግ፣ የፍትሕ ሂደቶች የደረሱበትን ሁኔታ መረጃ መስጠት፣ ሀሳባቸውን መስማትና በዋናነት አካላዊ፣ ማኅበራዊና ስነ ልቦናዊ የምልሰት እርምጃዎችን መውሰድና ሀሳብ መስጠት ለተጎጂው የሚደረግ ጥበቃ ሆኖ በሀገራት ላይ የተጣለ ግዴታ እንደሆነም ዶ/ር በላነይነህ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሕግ ትምህርት ቤት የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ር ጌትነት ደባልቄ ፕሮጀክቱ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂዎች ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትን ዓላማ ያደረገ ሲሆን ይህንንም ለማሳካት በቀጣይ ሁሉም የሕግ ትምህርት ቤት መምህራን በየማዕከላቱ በመሄድ በሚወጣው መርሃ ግብር መሠረት የንቃተ ሕግ ትምህርት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚሠሩና የምክር አግልግሎት፣ የሕግ ድጋፍ ዝግጅትና ወክሎ በመከራከር ጉዳት ለሚደርስባቸው አካላት አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡

የጋሞ ዞን ፍትሕ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጤናሁን ጨርቆስ እንደገለጹት ችግሩ በጣም ሥር የሰደደ በመሆኑ በፕሮጀክቱ ተሳታፊ የሆኑ ባለድርሻ አካላት በቀጣይ የድርሻቸውን ወስደው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተጀመረው ሥራም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በተለይ የሀገር ሽማግሌዎችንና የሐይማኖት አባቶችን በማሳተፍ ንቃተ ሕግ ሊፈጠር እንደሚገባና ፍትሕ መምሪያውም በጋራ እንደሚሠራ ጠቁመው ፍትሕ ሚኒስቴርም ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ለሚመለከተው አካል እንዲያደርስ  እንዲሁም  የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍልሰት ያለበት በመሆኑ የጀርመን ልማት ኤጀንሲ በልዩ ትኩረት ውጤት ሊያመጣ የሚችል ሥራ እንዲሠራ እገዛቸው እንዳይለያቸው ጠይቀዋል፡፡  

በፕሮግራሙ የማኅበራዊ ጉድኝት መምሪያና ጽ/ቤቶች፣ ሴቶችና ሕጻናት ጽ/ቤትና መምሪያ፣ የዞኑ ፖሊስ ጽ/ቤትና መምሪያ፣ የፍርድ ቤት ባለሙያዎችና ዳኞች፣ የወረዳ ፍትሕ ጽ/ቤት፣ ከኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዲሁም ከጀርመን ልማት ኤጀንሲ ባለሙያዎችና አሠልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት