Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር በደቡብና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በተመረጡ ስድስት ከተሞች ውስጥ በሚኖሩ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ላይ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት የስርጭት መጠን፣ መንስዔዎች እና የሚያስከትለውን ጉዳት አስመልክቶ የሠራውን ጥናት ሚያዝያ 10/2016 ዓ/ም በሶዶ ከተማ ለባለድርሻ አካት ይፋ አድርጓል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ጥናቱ እንዲሠራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ዩኒቨርሲቲው ውድድሩን በማሸነፉ ዘጠኝ አባላት ያሉት የምርምር ቡድን አቋቁሞ 1.5 ሚሊየን ብር በመመደብ  ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በራሱ ተነሳሽነትም ሆነ በሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ጥሪዎች በጋራና በተናጠል የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ ተስፋ የሚጣልባቸውን ምርምሮች እንደሚያካሂድ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ይህም ጥናት ችግርን መነሻ በማድረግ ከሚመለከተው አካል ጋር ተጣምሮ የሠራው ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም በጥናቱ የመፍትሔ ሃሳብ አስቀምጦ ከማለፍ ባሻገር ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ምርምሩን ለኅትመት ማብቃትና ለሰፊው ኅብረተሰብ ማሳወቅ እንዲሁም ችግሩን ለመቅረፍ ከክልሉ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮና ከሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዋኖ ዋኖሌ በክልሉ ያለውን የአደንዛዥ ዕፅ ስርጭት መጠንና ተያያዥ ጉዳዮች በጥናት ለማወቅ ቢሯቸው ባቀረበው ጥሪ መሠረት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የችግሩን ስፋትና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በጥሩ ሁኔታ የሚያሳይ ጥናት ሠርቶ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡ በጥናቱ የተገኘው ውጤት የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት በክልሉ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ የሚጠቁም ነው ያሉት የቢሮ ኃላፊው የጥናት ውጤቱንና በውይይት መድረኩ የተነሱ ሃሳቦችን ይዘን በቀጣይ የጋራ ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ እንሠራለን ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ብርሃኑ አላምረው የጥናት ውጤቱን ሲያቀርቡ እንደገለጹት የአደንዛዥ ዕፅ ተጋላጭነት እንደሚታይባቸው በተገመቱ ጂንካ፣ አርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ዲላ፣ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተሞች ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ በከተሞቹ ዕድሜያቸው ከ10-29 የሆኑ በአጠቃላይ 2040 አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች እንዲሁም 187 የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የሴክተር ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን 756ቱ (37.1 በመቶ) ያህሉ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጥናቱ አሳይቷል ብለዋል፡፡

የሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ት/ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ባይሳ ፈዬ በበኩላቸው ጥናቱ በተደረገባቸው ከተሞች አፍላ ወጣቶችንና ወጣቶችን ወደ ዕፅ ተጠቃሚነት ከሚገፉ ምክንያቶች መካከል አደንዛዥ ዕፅ የሚጠቀም የቤተሰብ አባል መኖር፣ የቤተሰብ ግጭትና መለያየት፣ የቤተሰብ ክትትል ማነስ፣ የጓደኛ ግፊት፣ የግንዛቤ ችግሮች፣ የአደንዛዥ ዕፆች በቀላሉ መገኘት፣ በቂ የሥራ ዕድል አለመኖር፣ የተወሰኑ አደንዛዥ ዕፆችን ማምረትና ማሰራጨት ላይ ግልጽ ፖሊሲ አለመኖርና የሕግ ቁጥጥር መላላት እንደሚገኙበት ጥናቱ መጠቆሙን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ባይሳ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ወደ ዕፅ ተጠቃሚነት የገቡ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ለአካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሌሎችም ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡ ችግሩ ከግለሰብ እስከ ሀገር የሚያስከትለው ጉዳት አሳሳቢና የተቀናጀ እርምጃ የሚጠይቅ በመሆኑ ጥናቱ ለዕፅ ተጠቃሚዎች፣ ቤተሰቦች፣ ዕፅ ነጋዴዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ ሕግ አውጪዎችና አስፈጻሚዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሥነ ልቦና ባለሙዎች እና ሌሎችም ባለድርሻዎች ዝርዝር ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን ዶ/ር ባይሳ ተናግረዋል፡፡

በጥናት ውጤት መግለጫ መድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላትና ተሳታፊዎች ለጥናት ቡድኑ አባላትና ለተቋማቱ ምስጋና አቅርበው ቢካተቱ ያሏቸውን ሃሳቦች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ጥናቱ ሁሉም የየራሱን ድርሻ መውሰድ በሚችልበት መልኩ ምክረ ሃሳቦችን ለእያንዳንዱ አካል በየዘርፉ ማቅረቡ ለአፈጻጸም አመቺ መሆኑን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ ጥናቱ ለፍሬ እንዲበቃ ተቀናጅቶ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት