Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከጋርዱላ ዞን ጋር በመተበበር የዲራሼ ብሔረሰብ ባህላዊ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ(ፊላ) በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ በተዘጋጀ ረቂቅ ትልመ ሃሳብ(Draft Project Proposal) ዙሪያ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሚያዝያ 12/2016 ዓ/ም ውይይት ተካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ  ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የደራሼ ብሔረሰብ ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ(ፊላ)ን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው ባለድርሻ ሆኖ በመሳተፉና አሻራውን ለማሳረፍ ዕድል በማግኘቱ ትልቅ ክብርና ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡ መሰል መድረኮች ትምህርታዊና ሙያዊ የሃሳብ ልውውጥ ከማድረግ ባሻገር የበርካታ ባህሎችና ቋንቋዎች ባለቤት የሆነውን ደቡብ ኢትዮጵያ ለማየት ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ዓለማየሁ ቅርስ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የሀገር ሀብት በመሆኑ ቅርሶችን በዘላቂነት ጠብቆና ተንከባክቦ ማቆየት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ ሚና ያለውና የማንነቱ መገለጫ ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ከመሆኗ ባሻገር በአፍሪካ ብሎም በዓለም ከፍተኛ ቅርሶች በማስመዝገብ ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት አንዷ መሆኗን በመጥቀስ ቅርሶች በግባቡ ከተጠቀምንባቸው ለተለያዩ ሀገር በቀል ዕውቀቶች በተለይ ለሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ጥበብ፣ እደ ጥበብ፣ ማኅበራዊ መስተጋብር እና ለሳይንስና ፍልስፍና መሠረት መሆናቸውን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲንና የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር መስፍን መንዛ በዲራሼ ሕዝብ ዘንድ ፊላ ከመወደዱ በላይ በግብርና፣ ደስታ፣ ሐዘንና ሌሎችም ሁለንተናዊ መስተጋብሮችና  ከሕዝቡ ማንነት ጋር የተጋመደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፊላ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ከባለድርሻ አካላት ግብአት ለማሰባሰብና በጥር 2015 ዓ/ም በተፈረመው የአራትዮሽ ስምምነት መሠረት ወደ ተግባር ለመግባት የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልና የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ፍሬው ተስፋዬ እንደገለጹት ከቀርከሃና ከሸምበቆ የሚሠራው የሙዚቃ መሣሪያ/ፊላ በዲራሼ ብሔረሰብ በተለያዩ ማኅበራዊ ሁኔታዎች ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ይህ ባህላዊ መሣሪያ በባህላዊ ልምምዳቸው እና በስብሰባዎቻቸው ውስጥ ወሳኝ ሚና ያለው ሲሆን ከ24-32 በሚደርሱ ሰዎች ከአምስት ሳ.ሜ እስከ አንድ ሜትር አማካይ ቁመት ባላቸው ቀርከሃ እና ሸንበቆ የሚበጁ በአንድ በኩል ክፍት በሌላው በኩል ድፍን የሆኑ የትንፋሽ መሣሪያዎች ስብስብ ነው ብለዋል፡፡

የኢፌዴሪ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ዶ/ር ታደለ ሰለሞን እንደገለጹት ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና የብዝኃ ባህል ሀገር መሆኗን ጠቅሰው የዲራሼ ሕዝብ ካሉት የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የዘመናት ታሪክ መገለጫ የሆነው ፊላ አንዱ ነው ብለዋል፡፡ የፊላ ቅርስ ጥናትን በተመለከተ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ተመራማሪዎችንና በጀት በመመደብ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በቅርበት እየተከታተለ እንደሚያሠራና ከውይይቱ የሚገኙ ግብአቶችን በመውሰድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ዶ/ር ታደለ ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ዱባለ ቢሮው በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የወላይታ ባህላዊ የዘመን መለወጫ በዓል ‹‹ጊፋታ››፣ ‹‹ጋሞ ዱቡሻ››ና ‹‹ዱቡሻ ዎጋ›› እንዲሁም የዲራሼ ‹‹ፊላ››ን በዩኔስኮ ለማስመዘገብ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት፣ ከኢትያጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና ከዞኖች ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር የራሱን ድርሻ ለመወጣትና የማኅበረሰቡን ዕውቀት ለማሸጋገር ለሚያደርገው ጥረትም አመስግነዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥናት ጥበቃና ልማት ቡድን መሪና የጥናቱ አቅራቢ አቶ ሙሉነህ ተፈራ የዲራሼ ሙዚቃ መሣሪያ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በአራቱ ተቋማት የተዘጋጀውን ጥናት ተወያይቶ አጽድቆ ወደ ሥራ ለመግባት የጋራ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ቅርሱ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች እንዲሁም የሕዝብ ንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ አቶ ሙሉነህ ጠቁመዋል፡፡

የጋርዱላ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ኩናሎ እንደገለጹት ፊላ ለዲራሼ ሕዝብ ለዘመናት በመላው ኢትዮጵያ ልዩ መለያውና መታወቂያው፣ በችግርና በፈተና ጊዜ በአንድነት መቆምን፣ እኩልነትና አካታችነትን፣ የደስታ መግለጫ፣ የሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለዲራሼ ሕዝብ መሠረታዊ እሴት ማሳያ እና ምስጋናና ምርቃት  ማቅረቢያ መሣሪያ ነው፡፡  ፊላ በየዘመናቱ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ የቆየና የዲራሼ ባህላዊ ቅርሶችን በመወከል የዲራሼ ሕዝብ ማንነት መገለጫ ነውም ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይድ አሕመድ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በ2015 ዓ/ም በተፈራረመው የአራትዮሽ መግባቢያ ስምምነት መሠረት ፊላን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ሥራ ለመጀመር የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ቅርሱ እንዳይጠፋ በቀጣይ ሦስት ዓመታት በሚከናወነው ጥናት ዩኒቨርሲቲያችን እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ጠንክሮ እንደሚሠራ ተናግረው ኢንስቲትዩቱ ‹‹ጋሞ ዱቡሻና ዱቡሻ ዎጋ›› እና ‹‹ፊላ የሙዚቃ ክዋኔ››ን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የማኅበረስብ ንቅናቄ መጀመሩንና በቀጣይም  በክልሉ የሚገኙ ሌሎች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በጥናትና ምርምር በመለየት በዓለም ደረጃ ለማስተዋወቅና በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በአስተያየቶቻቸው ፊላ ለማኅበረሰቡ ትልቅ የገቢ ምንጭ ሆኖ ማገልገል እንዲችል የጥናትና ምርምር ተግባራት በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት