የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ በደቡብ ኦሞ ዞን ያንጋቶም ወረዳ በሚነገረው የኩዌጉ ቋንቋና ባህል ስነዳ እና ትንተና ላይ ጥናት ለማካሄድ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሚያዝያ 12/2016 ዓ/ም የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የምርምር ዋና ዳይሬክተርና የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ለጥናቱ 1.75 ሚሊየን ብር መመደቡንና በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልጸው የትብብር ፕሮጀክት እንደመሆኑ ባለድርሻ አካላት በመናበብና በልዩ ትኩረት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ ደበሌ ኮሌጁ በዩኒቨርሲቲው አካባቢ በሚሠሩ በርካታ ጥናትና ምርምሮች ላይ በትኩረት እንደሚሳተፍ አስታውሰው የቋንቋ ስነዳ ሥራ ከክልሉ ብዝኃነት አኳያ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ቋንቋውን ሰንዶ ለቀጣይ ትውልድ ለማሻገር ኮሌጁ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የእንግሊዝኛ ቋንቋ ት/ክፍል መምህርና የፕሮጀክቱ ዋና ተማራማሪ ዶ/ር ዳኘው ማቸ በዞኑ የመጥፋት አደጋ ላይ ካሉ ቋንቋዎች አንዱ ኩዌጉ በመሆኑ ቋንቋውን ከመጥፋት ለመታደግና ሰንዶ ለትውልድ ለማሻገር ታልሞ ጥናቱ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዳኘው በጥናቱ ስድስት ተመራማሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን የቋንቋውን ሰዋስው፣ የማኅበረሰቡን ባህሎች፣ ሥነ ቃልና ትወና፣  መዝገበ ቃላት እና ለመማሪያነት የሚውሉ ውስን ሰነዶችን ማዘጋጀት ላይ በትኩረት ይሠራል፡፡ ቋንቋውን መሰነድና ማቆየት መቻል በቋንቋውና በባህሉ ውስጥ የተካተቱ በርካታ ሀገረሰባዊ ዕውቀቶችን ለማሻገርና ለፖሊሲ የሚሆን ግብዓት ለማቅረብ እንደሚረዳ ዶ/ር ዳኘው ተናግረዋል፡፡

የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ጽ/ቤት አስተባባሪና የጥናቱ አባል መ/ር ታፈሰ ዋልኤ በበኩላቸው ቋንቋውን መሰነድ ባለመቻሉ የቋንቋው ተናጋሪዎች የጠፉበትና የሞቱ በርካታ ቋንቋዎች እንዳሉ አስታውሰው የአንድን ማኅበረሰብ ቋንቋ መታደግ አስተሳሰብ፣ ፍልስፍናና ባህልን መታደግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መ/ር ታፈሰ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው መገኘቱ በክልሉ እየሞቱ ያሉ ቋንቋዎችን ለመታደግ ትልቅ ዕድል የሚፈጥርና የክልሉን ማኅበረሰብ የቋንቋ ስነዳ ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ዞን ም/ቤት ዋና አፈ ጉባኤና የአስተዳዳሪው ተወካይ አቶ ሎስንዴ ሎኛሱዋ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት የኩዌጉ ቋንቋና ባህል ላይ ጥናት ለማካሄድ መታሰቡ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ዩኒቨርሲቲው በዞኑ ያሉ ቋንቋዎችና ባህሎች እንዳይጠፉ ለመታደግ ለሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በቀጣይ ባሉ ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

አስተያየት የሰጡ የኩዌጉ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተናጋሪው ቁጥር እያነሰ በመምጣቱ እንዲሁም ከሌላ አካባቢ መጥተው በሚሰፍሩ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች ምክንያት የቋንቋው በሌላ መቀየጥና መዋጥ ትክክለኛውን ቋንቋ ለማስቀጠል አዳጋች ሆኗል ብለዋል፡፡ ቋንቋው ተጠንቶና ተሰንዶ መቀመጡ ለቀጣይ ትውልድ ለማሻገርና አዲስ የሚመጣ አካል በቀላሉ አንብቦ ሊማረውና ሊረዳው የሚያስችል በመሆኑ ትልቅ ደስታን እንደፈጠረላቸውና ለሥራው ስኬት በሙሉ ኃይል እንደሚተጉም ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተወካይ፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ም/ቤት አፈ ጉባኤ፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ፣ የያንጋቶም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪና ተወካይ፣ የያንጋቶም ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክና ምርምር ም/ፕሬዝደንት፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር፣ የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ዲን፣ የምርምር ቡድኑ አባላት እና የኩዌጉ ብሄረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት