Print

የኢትዮጵያ ህዋ ሣይንስ ማኅበር የበላይ ጠባቂና የእንጦጦ ህዋ ምርምርና ልዩ ማሠልጠኛ ማዕከል የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተፈራ ዋልዋ በጉጌ የህዋ ሣይንስ ምርምር ማዕከል ቅድመ አዋጭነት ጥናት ሂደት ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር መስከረም 16/2012 ዓ/ም ውይይት አካሂደዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሲያካሂድ የነበረው የምርምር ማዕከሉ የቅድመ አዋጭነት ጥናት መጠናቀቁ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

አቶ ተፈራ ዋልዋ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት የጉጌ ህዋ ሣይንስ ምርምር ማዕከል እንደ አገር ከተያዙ 3 ብሔራዊ ፕሮጀክቶች መካከል ሲሆን ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያውን የቅድመ አዋጭነት ጥናት መጨረሱ እንዳስደሰታቸውና የጥናት ውጤቱ ወደ ኢትዮጵያ የህዋ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተልኮ ተገምግሞ አስፈላጊ ማሻሻያዎች ተደርገው ሁለተኛው የአዋጭነት ጥናት ሊጀመር ይገባል ብለዋል፡፡

መንግሥት ለህዋ ሣይንስ ምርምር ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ተፈራ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም የመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ተቋቁሞ የነበረውን የማኅበሩን ቅርንጫፍ ማጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በበኩላቸው ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰው ማኅበሩን በማጠናከርና ሁለተኛውን የአዋጭነት ጥናት በመጀመር ለፕሮጀክቱ እውን መሆን እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡