Print

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የብዝሃ-ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከልና የእንሰትና የመድኃኒት ዕፅዋት ምርምርና ጥበቃ ፓርክ የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር በጠበቀ መልኩ የምርምር ሥራዎችን እየከናወነ ነው፡፡

የብዝሃ-ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል ዳይሬክተርና የሆርቲካልቸር ት/ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰይፉ ፈቴና የምርምር ማዕከሉ በዋናነት የዘር ምንጭ ሆኖ ለምርምርና ለማስተማሪያነት እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር በጠበቀ መልኩ የእንሰት ዝሪያዎችን በመንከባከብና በመጠበቅ እንዲሁም በእንሰት ዝሪያዎች ላይ የሚከሰቱ አንዳንድ ችግሮችን በሳይንሳዊ መንገድ ጥናትና ምርምር በማካሄድ በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየተሠራ ነው፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዶርዜ እንሰት ፓርክ በ2005 ዓ/ም የእንሰት ጥበቃ ፓርክ በመሆን የተመሠረተ ሲሆን ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ የእንሰትና የባህላዊ መድኃኒት ዕፅዋት ምርምር እና ጥበቃ ፓርክ ሆኖ በብዝሃ-ሕይወት ምርምር ማዕከል ሥር ተቋቁሟል፡፡ ተ/ፕ ሰይፉ እንደገለጹት እንሰት ለጋሞ ደጋማ አካባቢ ማኅበረሰብ የኢኮኖሚው ዋልታና የምግብ ዋስትና መሆኑ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በሽታን ጨምሮ በተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት የእንሰት ዝሪያዎች ከአካባቢው ሥነ-ምህዳር እየጠፉ እንዲሁም ምርትና ምርታማነት እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመታደግ ከዘረ-መል መጠበቂያ መንገዶች አንዱ በሆነው የመስክ ዘረ-መል ባንክ ዘዴ በመጠቀም በምርምር ማዕከሉ 55 የእንሰት ዝሪያዎችን በመሰብሰብ የመንከባከብና የመጠበቅ ሰፊ ሥራዎች እየተካሄዱ ሲሆን በቀጣይም ምርምር በማድረግ የማኅበረሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የማዕከሉ ዳይሬክተር አክለው እንደተናገሩት ከዚህ በፊት በዶርዜ እንሰት ፓርክ 40 የእንሰት ዝሪያዎች የሚገኙ ሲሆን ተጨማሪ ሌሎች ዝሪያዎችን ከቦንኬ፣ ከዳውሮና ከአረካ የምርምር ጣቢያዎች በማምጣት በአሁኑ ሰዓት 55 የእንሰት ዝሪያዎች ይገኛሉ፡፡

እንሰት ቅጠሉ በእርጥበቱ ኮባ፣ ሲደርቅም ገመድ፤ ግንዱ ሲደርቅ የቆጮና ቡላ ማዘጋጃና መጠቅለያ፣ ለወተት መናጫና ሌሎች መሰል ዕቃዎች መሸፈኛ፣ ለቅቤ መያዣ ሁነኛ መገልገያ ሲሆን በእርጥበቱ ደግሞ ተፍቆ ቆጮና ቡላ ነው፡፡ እንሰት አምቾው ተቀቅሎ በቀጥታ ለሰው ምግብ እንዲሁም የቆጮ እርሾ ማዘጋጃ ነው፡፡ አምቾ በደንብ እንዲደቅ ተደርጎ ተዘጋጅቶ በተፋቀው የእንሰት ግንድ በመቀላቀል ጥራት ያለው የቆጮ ምርት እንዲዘጋጅ የሚያግዝ የእንሰት ክፍል ነው፡፡ የእንሰት ዝሪያዎች ወንዴና ሴቴ ተብለው የሚለዩ ሲሆን ወንዴ ዝሪያዎች በባህሪያቸው ቅጠላቸው ሰፋፊና ትልቅ ሆነው የሚያድጉ ሲሆኑ የሴቴ ዝሪያዎች ደግሞ የአካል መጠናቸው አነስተኛና በብዛት ለተለያዩ በሽታዎች መድኃኒት ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

እንሰት ድርቅን የሚቋቋም ዕፅ በመሆኑ የዝናብ ዕጥረት በሚፈጠርበት ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ለሰውና ለእንስሳት መኖነት የሚፈለግና ከቅጠል እስከ ሥሩ ያለው ለቆጮ አገልግሎት የማይውል ትራፊ በቆጮ ዝግጅት ወቅት ለእንስሳት ምግብነት የሚውልና ለተለያዩ ጉዳዮች ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጥ ተክል ስለሆነ የዘርፉ ምርምሮች ተጠናክረው ቢቀጥሉ በምግብ ዋስትና ስትራቴጂ የማኅበረሰብ ተጠቃሚነቱ የጎላ ይሆናል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የዩኒቨርሲቲው የብዝሃ-ሕይወት ምርምርና ጥበቃ ማዕከል በሥሩ የእንሰትና የመድኃኒት ዕፅዋት ምርምርና ጥበቃ ፓርክ ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ በመቋቋሙ በርካታ የመድኃኒት ዕፅዋት በመሰብሰብ የመንከባከብና የመጠበቅ

ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ በዚህም መሠረት እንደ አርትሚዝያ፣ ቀበርቾ፣ አዛምር፣ ጦስኝ፣ ናትራ፣ ጤና አዳም፣ ካቲካላ፣ ዳማካሴ፣ ኮሶ፣ የሥጋ መጥበሻ፣ እንቆቆ፣ እንዶድ፣ ጥቁር እንጨት፣ ወይራ፣ አባሎ፣ ሾላ ዋርካና ሌሎችም የመድኃኒት ዕፅዋት ዝሪያዎች በምርምር ማዕከሉ ተሰብስበው እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አያይዘውም በባህላዊ መድኃኒት ዕፅዋት ዙሪያ የሚካሄደው ምርምር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማርካት የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎችን በተያዘ የጊዜ ገደብ በጥራት ለማከናወን ተግዳሮት ከሆኑ አበይት ችግሮች መካከል የዙሪያ አጥር አለመኖር፣ የዲች አለመሠራት፣ የባለሙያ ዕጥረት፣ የትራንስፖርት መኪና አለመኖር፣ መብራትና ውሃ አለመኖርና የማዕከሉ ሕንፃ አገልግሎት ላይ እንዲውል አስፈላጊ ፈርኒቸር አለመሟላት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት