Print

በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ የጌጣጌጥ ማዕድናት ምርትና ግብይት ዘርፍ ለባለድርሻ አካላት ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫና የምክክር መደረክ ላይ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የማዕድን አለኝታ ጥናት ማካሄዱ ተገልጿል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ


የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደክዮስ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ በሁለት ዓይነት መንገድ ጥናቶችን እያካሄደ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው የጥናት ዓይነት ዩኒቨርሲቲው በራሱ ዕቅድ፣ በጀትና ጊዜ የሚያካሂደው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመንግሥትና በተለያዩ ተቋማት ጋባዥነት ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው መነሻ ሃሳቦች ላይ የሚካሄድ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው በ2012 ዓ/ም በጋሞ ዞን የተሠራው ጥናት ውጤት ማሳየት መጀመሩን ተናግረው ዘንድሮም በክልሉ ጥያቄ መሠረት በደቡብ ኦሞና ኮንሶ ዞኖች ያሉ ማዕድናትን በዓይነት ለይቶ ለክልሉ ለማሳወቅ ጥናቱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ጂኦሎጂ ት/ክፍል መምህርና የጥናት ቡድኑ አባል አቶ አገኘሁ ቦርኮ በኮንሶና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ከፍተኛ ጥራትና ስፋት ያላቸውና ለኢንደስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የጋሞ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ የማዕድናቱ መገኘትና ወደ ሀገር ኢኮኖሚ መቀላቀል መጀመር መልካም ቢሆንም በባህላዊ መንገድ የሚያወጡ ወጣቶችን ለመደገፍና የሀገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ የተሻሉ ማሽኖች የሚገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የተሻለ ዕውቀትና አቅም ያላቸው ባለሀብቶችን በመጋበዝ ቀጣይነት ባለው መንገድ ኢኮኖሚውን ለመቀላቀል የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ አርባ ምንጭ፣ ወላይታ ሶዶና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናታዊ ጹሑፎችን ያቀረቡ ሲሆን የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ ባለሀብቶችና በማኅበራት የተደራጁ ወጣቶች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት