የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት የአምሳለ ፍርድ ቤት ፍጻሜ ውድድር ጥር 23/2016 ዓ/ም ያካሄደ ሲሆን ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ውድድር ኢትዮጵያንና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን በመወከል በታንዛንያ አሩሻ በተደረገው ጠቅላላ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ተሳትፈው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ውድድሩን አሸንፈው ለመጡ ተማሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት የሕግ ት/ቤት ዩኒቨርሲቲው ካሉት ጠንካራ ትምህርት ቤቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የአመራሩ፣ የተማሪዎቹና የመምህራኑ ጠንካራ ሥራ ድምር ውጤት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ አክለውም ት/ቤቱ በመውጫ ፈተና ውጤታማ መሆኑ፣ አቅም ለሌላቸው የአከባቢው ማኅበረሰብ ክፍሎች ነጻ የሕግ ድጋፍ መስጠቱ፣ የአምሳለ ፍርድ ቤት ማኅበር በማቋቋም ዓመታዊ አምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር በቀጣይነት ማካሄዱ እና መሰል ተግባራት ማከናወኑ ፍትህንና መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር ትልቅ ማኅበራዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል፡፡ ት/ቤቱ በውድድሩና በሌሎች ዘርፎች የመጣውን ውጤት ማስቀጠል እንዳለበት እንዲሁም የዕለቱ ተወዳዳሪዎችም የተሻሉ ተሞክሮችን በመውሰድ ለቀጣይ ሀገራዊና አህጉራዊ ውድድሮች በትጋት እንዲዘጋጁ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ  የሕግ ት/ቤት ጠንካራና ለሌላው አርዓያ  ሆኖ የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸው ያደጉ ሀገራት ዜጎች ተከባብረው ለመኖር የቻሉት ስለሕግና ፍትህ ግንዛቤ ከሕጻንነት ዕድሜያቸው ጀምሮ መሥራት ስለቻሉ ሲሆን በእኛም ሀገር የሕግና ፍትህ ንቃተ ኅሊና በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ ከሕጻንነት ጊዜ ጀምሮ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡  

የሕግ ት/ቤት ዲን አቶ ዳኛቸው ወርቁ ት/ቤቱ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፎች መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ እንዳለ ጠቁመው የአምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር የተግባር ልምድ ልውውጥ የተማሪዎችን የምስለ ችሎት ውድድር ብቃት ለማሳደግ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ ዲኑ መድረኩ ዩኒቨርሲቲያችንና እና ሀገራችንን ወክለው በአህጉር ደረጃ ተወዳድረው ከፍተኛ ውጤት ያመጡትን ተማሪዎች ለመሸለምና ለማበረታታት፣ ከሳምንት በፊት ሲካሄድ የነበረውን የአምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር አሸናፊ በመለየት ለመሸለም እንዲሁም የአምሳለ ፍርድ ቤት ማኅበር ዓላማን ለማስተዋወቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሕግ ት/ቤት ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና፣ የአምሳለ ችሎትና የክሊኒካል ኮርስ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ክንፈ እንደተናገሩት በሀገር አቀፍ ውድድር ዋንጫ ያመጡትንና በታንዛንያ አህጉራዊ ውድድር ከፍተኛ ውጤት ያመጡትን መሸለምና ዕውቅና መስጠት ሌሎች የነሱን ተሞክሮ አይተው ለቀጣይ ለሚኖረው ዓለም ዓቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች እንዲነቃቁ ያደርጋል፡፡ ኃላፊው አክለውም በዘንድሮው አምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር እየተሳተፉ ከሚገኙ ስድስት ቡድኖች የእርስ በእርስ ማጣሪያ ውድድሩን አልፈው ለፍጻሜ የበቁት ቡድኖች ተለይተው መቅረባቸውንና ይህም ተማሪዎቹ  ለውድድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ፣ የሙግትና የመከራከር አቅማቸውን እንዲያጎለብቱና የመረዳት ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ  ያግዛል ብለዋል፡፡

 

በመርሃ-ግብሩ በታንዛንያ አህጉራዊ አምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሦስት ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው ስማርት ስልክ እና ሰርተፊኬት፣ በዘንድሮው አምሳለ ፍርድ ቤት የፍጻሜ ውድድር የመከራከሪያ ሃሳባቸውን አቅርበው በተሰየሙ ዳኞች ፊት አሸናፊው ተለይቶ 1 እና 2ለወጡ ሁለት ቡድኖች የገንዘብና የሰርተፊኬት ሽልማት እና በዙሩ ላይ አንደበተ ርቱዕ ለተባለችውና በጽሑፍ ከቀረቡ ሃሳቦች ምርጡን ሃሳብ ያቀረበው ቡድን ተለይተው የገንዘብና የሰርተፊኬት ሽልማት እንዲሁም ለውድድሩ ዳኞች ሰርተፊኬት ተበርክቷል፡፡ 

በመርሃ ግብሩ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የትምህርት ቤት ዲኖች፣ የሕግ ትምህርት ቤት መምህራን፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት