አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር ‹‹Building Information Management/BIM›› በሚል ርእስ ለአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ እና ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች መምህራን፣ ለዩኒቨርሲቲው ፋሲሊቲ አስተዳደርና የግንባታ ጽ/ቤት ባለሙያዎች ከጥር 13 - 30/2016 ዓ/ም የግንባታ ሞዴሊንግ ቴክኖሎጂን አስመልክቶ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያደረገች ካለችው ማሻሻያዎች አንዱ የግንባታ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው የግንባታ ሞዴሊንግ ቴክኖሎጂ ከዚህ ቀደም በግንባታ ሞዴሎች በትክክል አለመሠራት ምክንያት የሚባክነውን ተጨማሪ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ም/ሳይንቲፊክ ዳይይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን ንዋይ በበኩላቸው ሠልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ለማስፋት ማንበብና መለማመድ ብሎም በቀጣይ ሌሎች ባለሙያዎችንና ተማሪዎችን ማሠልጠን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ የፌዴራል ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በተለያዩ ፕሮጀክቶች የዩኒቨርሲቲውን ባለሙያዎች በማሳተፍ በጋራ እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ከፍያለ እንደገለጹት ከ2017 ዓ/ም ጀምሮ በዘርፉ ያልሠለጠነ ባለሙያ በግንባታ ዘርፍ እንዳይሳተፍ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በዩኒቨርሲቲው የሚያስተምሩ መምህራን የቴክኖሎጂው ክሂሎት እንዲኖራቸው፣ ለአዲስ ተመራቂ ተማሪዎች ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅና በፋሲሊቲ አስተዳደርና በግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የሠለጠኑ ባለሙያዎች እንዲኖሩ ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡

በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አሠልጣኝ ኢ/ር ፈለቀ አሰፋ ሥልጠናው ‹‹BIM - Architectural››፣ ‹‹BIM-Structural››፣ ‹‹BIM-MEP-Mechanical››፣ ‹‹BIM-MEP Plumbing››፣ ‹‹BIM-MEP-Electrical›› እና ‹‹BIM-Project Management›› በሚሉ ይዘቶች መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ዓላማውም ሞዴል ተሠርቶ በመተቸት ወደ ሥራ ለመግባት፣ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ የሚነሱ ትችቶችን ለመቀነስና ለድጋሚ ሥራ የሚወጣውን የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪ ማስቀረት ነው ያሉት አሠልጣኙ የግንባታ ሥራዎች ወደ ተግባር ሲገቡ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የዲዛይን፣ የበርና መስኮት፣ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ የመጸዳጃ ቤት እና ሌሎች ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ክሂሎት ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል፡፡

የሲቪል ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርትና የሥልጠናው ተሳታፊ መምህርት ስለእናት ድሪባ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው የመምህራንን የግል ክሂሎት ከማሳደጉም በላይ ለተማሪዎቻችን የተሻለ ዕውቀት ለመስጠት የሚጠቅም ነው ብለዋል፡፡

ሌላኛው የሥልጠናው ተሳታፊ የፋሲሊቲ ልማት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መተኪያ አዛዥ ሥልጠናው በግንባታ ዘርፍ የዲዛይን፣ ከዲዛይን ጋር ተያይዞ ሊመጡ የሚችሉና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም የግንባታ መጓተትን ለማስቀረት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት