Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ10 ደቂቃ አንድ ኩንታል በቆሎ መፈልፈል የሚችል ማሽን ሠርቶ የካቲት 02/2016 ዓ/ም በጋሞ ዞን ካምባ ዙሪያ ወረዳ ጋርሳ ሀኒቃ ቀበሌ ሶቦ መንደር ለሚገኙ አርሶ አደሮች ለሙከራ አቅርቧል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ የኢንደስትሪ ትስስር ትኩረት ቴክኖሎጂን መፍጠር፣ መሞከርና ማሸጋገር መሆኑን ገልጸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለሙከራ የተሠራው የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን ውጤታማነቱን በማረጋገጥ በማኅበረሰብ ጉድኝት በኩል በስፋት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ቶሌራ አርሶ አደሮቹ የቴክኖሎጂ ውጤቱን በአግባቡና በእንክብካቤ በመያዝ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስበው ማሽኑን በመጠቀም ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመለየት ለዩኒቨርሲቲው ቢያሳውቁ ቴክኖሎጂውን አሻሽሎ ለማቅረብ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህር ከሆኑት አቶ አዳነ ካሳ ጋር ቴክኖሎጂውን በጋራ የሠሩት የቴክኖሎጂ ሽግግር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር ፍራኦል በቃና የማሽኑን አጠቃቀምና ሊደረጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች አስመልክቶ ለተጠቃሚው አርሶ አደር ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት በተግባር እንዲለማመዱ አድርገዋል፡፡ በቀጣይ በቴክኖሎጂው ላይ የሚስተዋሉና ሊሻሻሉ የሚገቡ ነገሮችን ከተጠቃሚው አርሶ አደር አስተያየቶችን በመቀበልና ቴክኖሎጂው ላይ በመጨመር በተሻለ ሁኔታ ምቹ ሆኖ የሚቀርብ መሆኑን መ/ር ፍራኦል ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኑ የምርት ጥራት ተጠብቆ ብክነት ሳይገጥመው በአጭር ጊዜ ወደ ጎተራ ለማስገባት የሚረዳ በመሆኑ ያሉበትን ተግዳሮቶች በመለየት፣ ከተጠቃሚው አርሶ አደር አስተያየቶችን በመውሰድና ተግባራዊ በማድረግ በቀጣይ በተሻለ ሁኔታ ጥራቱ ተጠብቆ ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ሳቡራ ሻራ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች ያገኙትን የበቆሎ ምርት በእጃቸው ፈልፍለው ለማስገባት እና በወቅቱ ምርቱን ሰብስበው ለቀጣይ ለመዘጋጀት መቸገራቸውንና ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንዲያደርግ በጠየቁት መሠረት ምላሽ የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ሳቡራ ቴክኖሎጂው መምጣቱ የአርሶ አደሩን ችግር እንደሚያቃልልና በእጅጉ የሚደግፋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ግብርናን ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ቴክኖሎጂን መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት የካምባ ዙሪያ ወረዳ ም/አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓባይነህ ደቻሳ አካባቢው ቆላማ በመሆኑ አርሶ አደሮች ያገኙትን የበቆሎ ምርት በእጃቸው ፈልፍለው በወቅቱ ለማንሳት በከፍተኛ ሁኔታ መቸገራቸውን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው ትብብር እንዲያደርግላቸው በጠየቁት መሠረት አፋጣኝ ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው በወረዳው ሌሎች የሰብል ዓይነቶችና ፍራፍሬዎችም የሚመረቱ በመሆኑ መሰል የቴክኖሎጂ ድጋፎችን በማድረግና ምርጥ ዘሮችን በመስጠት የተጀመረውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀው በእነርሱ በኩል ቴክኖሎጂውን ወደ አርሶ አደሩ ለማሸጋገር በማስተማርና በመደገፍ እንሠራለን ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ እርሻ ዘርፍ ኤክስቴንሽን ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ጌዲዮን መንታ መፈልፈያ ማሽኑ አርሶ አደሩን ከምርት ብክነትና ከጥራት ጉድለት እንዲሁም ከአላስፈላጊ ወጪ የሚታደገው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በማሳው ላይ የተጀመረው ሥራ በጣም ስኬታማ እንዲሆንና አርሶ አደሩ ምርቱ ሳይባክን ጥራቱን ጠብቆ ለቤትና ለገበያ ማዋል እንዲችል በቀጣይ ቴክኖሎጂውን በአርሶ አደሩ መካከል በማኖርና በአግባቡ በመቀባበል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ይሠራልም ብለዋል፡፡ አቶ ጌዲዮን አክለውም ዩኒቨርሲቲው በተለያየ መንገድ ለኅብረተሰቡ አለኝታ በመሆን ችግሮችን እየፈታ በመሆኑ አመስግነው ቴክኖሎጂው ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርስ የግብርና ባለሙያዎች ልምድ ወስደው ለሌሎች አርሶ አደሮች በማስተማርና ተጠቃሚ በማድረግ የማስፋፋት ሥራ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡

የቴክኖሎጂው የመጀመሪያ ተጠቃሚ በመሆኑ መደሰቱን የገለጸው ወጣት አርሶ አደር ቶማስ ገዛኸኝ ቴክኖሎጂው ድካምን በእጅጉ የሚቀንስ፣ ጊዜን የሚቆጥብና ለቀጣይ ዘር እንዲዘጋጁ የሥራ ተነሳሽነትን የሚጨምር በመሆኑ ሁላችንም በጥንቃቄ እንሠራበታለን ብሏል፡፡ አርሶ አደር ቶማስ ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ፈጥሮ ማሳ ድረስ ወርዶ በማሸጋገሩ ልባዊ ምስጋና አቅርቧል፡፡ በቀጣይም ማሽኑ በስፋት እንዲቀርብና አቅም ያለው በግሉ ገዝቶ የሚሠራበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ዩኒቨርሲቲውና የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት በመናበብ ቢሠሩ ምርታማ እንሆናለን ብሏል፡፡

ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት የቴክኖሎጂ ውጤቱ አርሶ አደሩን በእጅጉ የሚደግፍና ድካማቸውን የሚቀንስ በመሆኑ በተሻለ መንገድ አምርተው ያለምንም መንገላታት ምርታቸውን ለመሰብሰብና ትርፋማ ለመሆን እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡ ማሽኑን በመተሳሰብና በመደጋገፍ በአግባቡ በመጠቀም ወደፊት የተሻለ ኑሮ እንደሚመሩ አክለው ዩኒቨርሲቲው በተለያየ መንገድ ለሚያደርግላቸው እገዛና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡  

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት