የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማዕከል ከዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ት/ክፍል እና ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በጫሞ ካምፓስ ለሚገኙ 2ና 3 ዓመት የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ‹‹Social-Emotional Learning Program›› በሚል ርእስ ከየካቲት 17/2016 ዓ/ም ጀምሮ የ120 ሰዓታት ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሥልጠናው ‹‹Self-Awareness››፣ ‹‹Self-Management››፣ ‹‹Social Awareness››፣ ‹‹Relationship Skills›› እና ‹‹Responsible Decision Making›› በሚሉ ይዘቶች የሚሰጥ ሲሆን ዓላማውም የተማሪዎችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክሂሎት በማሻሻል በትምህርት አቀባበላቸው በመጎበዝ ውጤታማ እንዲሆኑ እንዲሁም የእርስ በእርስ መስተጋብራቸው እንዲጎለብትና በሕይወታቸው የተሻሉ ሰዎች እንዲሆኑ ማገዝ ነው፡፡

በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማዕከልና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ት/ክፍል በጋራ የተዘጋጀ የጽሑፍና የተግባር ፈተና ወስደው የማለፊያ ነጥብ ያገኙ ከተለያዩ ት/ክፍሎች የተወጣጡ 26 ተማሪዎች እና በፍላጎት ሥልጠናውን የሚወስዱ ሁለት የእንግሊዝኛ ት/ክፍል መምህራን በሥልጠናው ተሳትፈዋል፡፡ ሠልጣኞቹ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 5 እና 6 በአዲስ አበባ ከተማ ተገኝተው በሐረማያና ጅማ የኒቨርሲቲዎች መሰል ሥልጠና ከወሰዱ ተማሪዎች ጋር የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉ ሲሆን በመጨረሻም የምረቃ መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ የምስክር ወረቀት የሚወስዱ ይሆናል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ፕሮግራሞች ክትትልና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሠረቀ ብርሃን ታከለ፣ የማኅበራዊና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ም/ዲን አቶ ኤርምያስ በፈቃዱ፣ የእንግሊዝኛ ት/ክፍል ኃላፊ ዶ/ር አባተ አንጁሎ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማዕከል አስተባባሪ ዶ/ር መለሰ መንገሻ በሥልጠናው ማስጀመሪያ ፕሮግራም ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት