አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ክርስቲያን ኤይድ/Christian Aid/ እና ኤስኦኤስ ሳህል ኢትዮጵያ /SOS Sahel Ethiopia/ ከተሰኙ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከጋሞና ወላይታ ዞኖች ለተወጣጡ ማኅበራት ተወካዮችና ሥራ አጥ ወጣቶች ከጥር 29/2016 - የካቲት 15/2016 ዓ/ም በሁለት ዙሮች ከእንሰት ቃጫ እሴት የተጨመረባቸው ቁሳቁሶችን የሚያስችል ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በዩኒቨርሲቲው የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እንደገለጹት የእንሰት ቃጫ በባህላዊ መንገድ ለሚሠሩ ቁሳቁሶችና ለጂፕሰም ቦርድ መሥሪያነት ለሽያጭ ከመቅረቡ ውጪ በአብዛኛው ለሌላ አገልግሎት አይውልም፡፡ ከቃጫ እሴት ተጨምሮባቸው የተሻለ ዋጋ የሚያወጡና ለቤትና ለቢሮ ጌጣጌጥ እንዲሁም ለዕለት ከዕለት አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ማምረት እንደሚቻል የተናገሩት ዶ/ር አዲሱ ወጣቶቹ የቁሳቁሶቹን አሠራር በቂ ክሂሎት አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግና በዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻል የሥልጠናው ዓላማዎች ናቸው፡፡ አካባቢው ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለው እንደመሆኑ ወጣቶች ቱሪስቶችን ማዕከል ያደረጉ ምርቶችን አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ማድረግም ሌላኛው የሥልጠናው ትኩረት መሆኑን ዶ/ር አዲሱ ጠቁመዋል፡፡

ለሠልጣኞች ለሥራው የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን በመስጠት በቀጥታ ወደ ምርትና ሌሎችን ወደ ማሠልጠን እንዲገቡ እንደሚደረግ የጠቀሱት ዶ/ር አዲሱ መስኩ ለብዙ ሺህ ሥራ አጥ ወጣቶች አዲስ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያለው በመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር መሥራት ለሚፈልጉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የአብረን እንሥራ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በእንሰት ማምረት ሂደት ውስጥ ያሉ በርካታ ማነቆዎችን የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎችን አበልጽጎ ለማኅበረሰቡ እያደረሰ ሲሆን ከእንሰት ቃጫ እሴት የተጨመረባቸው ቁሳቁሶችን በማምረት ላይ የተሰጠው ሥልጠናም ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ጉልህ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ ዶ/ር ቶሌራ ለአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ ለሥልጠናው አስተባባሪዎች እና ለአሠልጣኞች ለሥልጠናው መሳካት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ ሠልጣኞች የሠለጠኑበት መስክ አዲስና ምንም ያልተሠራበት እንደመሆኑ ወጣቶቹ ቀጥታ ወደ ሥራ ከገቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ሠልጥኖ ወደ ሥራ አለመግባት ትልቅ ኪሳራ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ቴዎድሮስ ሠልጣኞቹ ሌሎች የአካባቢያቸውን ወጣቶች ጭምር በማሠልጠን ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የሥልጠናው አስተባባሪ ዶ/ር ይሄነው ውቡ ሥልጠናው በየቀኑ ለ9 ሰዓታት መሰጠቱንና ሠልጣኞች በከፍተኛ ትጋትና ፍላጎት ሲከታተሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሠልጣኞች በቆይታቸው ያገኙትን ክሂሎት በየጊዜው ለማዳበርና አዳዲስ ምርቶችን ለመፍጠር ሊተጉ እንደሚገባም መክረዋል፡፡

ከአሠልጣኞች መካከል ከጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ የመጡት ወ/ሮ ዓመቱ ተዘራ ከዚህ ቀደም ይህንን ሥልጠና በጃፓኑ ጃይካ አማካኝት መውሰዳቸውንና አሁን ላይ ከ80 የአካባቢው ሴቶች ጋር በማኅበር በመደራጀት ከቃጫ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ዓመቱ ከዚህ ቀደም ምንም እሴት ሳይጨመር ጥሬ ቃጫ ለገበያ በማቅረብ አነስተኛ ገቢ ያገኙ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን ከቃጫ ቦርሳ፣ ዘምቢል፣ የአበባ ማስቀመጫ፣ የፍራፍሬ ማቅረቢያና ሌሎች ቁሳቁሶች ሠርተው ለገበያ በማቅረብ የተሻለና ኑሯቸውን የቀየረ ገቢ እያገኙ ነው፡፡ ወ/ሮ ዓመቱ መስኩ አዋጭና ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት ያለበት መሆኑ በተግባር የታየ በመሆኑ ወጣቶቹ ከሥልጠናው በኋላ ቀጥታ ወደ ሥራ በመግባት የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለመቀየር እንዲተጉ መክረዋል፡፡

ከወላይታ ዞን ዳሞት ቡላሳ ወረዳ የመጣችው ሠልጣኝ ዘላለም አባተ በቃጫ ሥራ ላይ በማኅበር ተደራጅተው እየሠሩ ቢሆንም ከቃጫ ገመድ ከመሥራትና በጥሬው ከመሸጥ ባሻገር በዚህ መልክ በርካታ ቁሳቁሶች ይሠሩበታል ብላ አስባ እንደማታውቅ ተናግራለች፡፡ ከወላይታ ሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኮንስትራክሽን የትምህርት መስክ በደረጃ V መመረቋን የምትገልጸው ወጣት ዘላለም በሥልጠናው ከቃጫ ዘምቢል፣ ቦርሳ፣ መሶብ፣ ቀበቶ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማምረት እንደሚቻል በተግባር ማየቷን ገልጻለች፡፡ ሥልጠናውን ላዘጋጁ አካላት ምሥጋና ያቀረበችው ወጣት ዘላለም ከሥልጠናው መልስ ሌሎች የማኅበራቸውን አባላት በማሠልጠን በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን ዝግጁ መሆኗንም ተናግራለች፡፡

ከጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶርዜ ሆሎኦ ቀበሌ የመጣችው ሌላኛዋ ሠልጣኝ ፍቅርተ አበራ በበኩሏ ከቃጫ ውብ የሆኑ ጌጣጌጦችና የቤት ውስጥ ዕቃዎች ተሠርተው ማየቷና በተግባር መሥራቷ በእጅጉ እንዳስገረማት እንዲሁም የሥልጠና ዕድሉን ማግኘቷ እንዳስደሰታት ተናግራለች፡፡ ዶርዜና አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የቱሪስት ፍሰት ያለበት አካባቢ በመሆኑ ከሥልጠናው መልስ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን ለቱሪስቶች የሚሆኑ ጌጣጌቶችን ከቃጫ በማምረት ለሽያጭ ለማቅረብ ከወዲሁ ማቀዷንም ገልጻለች፡፡

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ለሠልጣኞች፣ ለአሠልጣኞችና ለሥልጠናው አስተባባሪዎች የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ከጉራጌ ዞን በመምጣት ሥልጠናውን ሲሰጡ ለቆዩ ሁለት አሠልጣኞች ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት