አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት፣ አሜሪካ ሀገር የሚገኘው አላባስተር ኢንተርናሽናል/Alabaster International እንዲሁም ኬንያ የሚገኙት ገርል ቻይልድ ኔትወርክ/ Girl Child Network እና ጆሞ ኬንያታ የግብርናና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ/ Jomo Kenyatta University of Agriculture and Technology በመተባበር ‹‹Enset Cultivation, Development and Utilization in Ethiopia and Kenya›› በሚል ርእስ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመው የጀመሩት ዓለም አቀፍ የምርምር ትብብር ፕሮጀክት እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. ጥር 01, 2023 ተጀምሮ ለሦስት ዓመታት የሚቆየው ፕሮጀክት ከአንድ መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ በጀት የተመደበለት ሲሆን በዋናነት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በ‹‹Jomo Kenyatta University of Agriculture and Technology›› የሚተገበርና በ‹‹Alabaster International›› እና ‹‹Girl Child Network›› በገንዘብ የሚደገፍ ነው፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በፕሮጀክቱን የሥራ እንቅስቃሴና አጠቃላይ ዓላማን ለማስገንዘብ እንዲሁም በኬንያ የነበረውን ቆይታ ልምድ ለማካፈል የተዘጋጀ የውይይት መድረክ የካቲት 14/2016 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሆርቲካልቸር መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ሳቡራ ሻራ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በሦስት ሀገራት የሚገኙ አምስት ተቋማትን ለአንድ ዓላማ ያስተሳሰረ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የምርምር ፕሮጀክት ነው፡፡ እንሰት ለምግብነት የሚውለው በኢትዮጵያ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ሳቡራ ተክሉ ከኢትዮጵያ ውጪ በምሥራቅ፤ ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ብሎም በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች በጫካ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥንና በሽታን ለመቋቋምና ለምግብነትም ሆነ ለሌሎች ግልጋሎቶች እንዲውል ለማድረግ ዘርፈ ብዙ የምርምር ሥራዎች ተጠናከረዉ መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡ በተለይ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የምግብ ዋስትና ችግር መፍትሔ እንዲሆን የሚያግዙ አዳዲስ ዕውቀቶችን ማበልጸግና ማውጣት የፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረት እንደሆነ ዶ/ር ሳቡራ ጠቁመዋል፡፡ እንሰት ድርቅን የሚቋቋም ተክል መሆኑ በተለምዶ የሚታወቅ ሲሆን ተክሉ ድርቅን ለምን ያህል ጊዜና እንዴት እንደሚቋቋምና የትኞቹ የእንሰት ዝርያዎች በተሻለ ሁኔታ ድርቅን እንደሚቋቋሙ መለየት የሚያስችል የመስክና የቤተ ሙከራ ጥናት ማድረግ ሌላኛው የምርምር ሥራው ትኩረት እንደሆነ ዶ/ር ሳቡራ ተናግረዋል፡፡ በኬንያና በኢትዮጵያ በጫካ ውስጥ እንሰት ይገኛል ያሉት ዶ/ር ሳቡራ እነዚህ ጫካ ውስጥ የሚገኙ የእንሰት ዝርያዎች የምግብ ይዘት እንዲሁም ድርቅንና በሽታን የመቋቋም አቅማቸውን በተለያዩ ሳይንሳዊ መንገዶች መፈተሽም ከምርምር ፕሮጀከቱ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

የእንሰት አጠውልግ በሽታ በየትኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኝ እንሰትን የሚጎዳና የሚያጠፋ እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ ከተክሉ የሚገኘውን ምርት የሚቀንስ ዋነኛ ችግር እንደሆነ የጠቆሙት ዶ/ር ሳቡራ ቲሹ ካልቸር /Tissue Culture/ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከበሽታ የጸዱ ችግኞች/Sucker/ ለአርሶ አደሩ አባዝቶ ለማሰራጨት የሚያስችል ፕሮቶኮል የማዘጋጀት ተግባር በምርምር ሥራው ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የጆሞ ኬንያታ የግብርናና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በቲሹ ካልቸር ዘርፍ ላይ የካበተ ልምድ ያላቸው ተመራማሪዎችና የተደራጀ ቤተ ሙከራ ያለው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የቲሹ ካልቸር ቤተ ሙከራ ለማቋቋም ለሚሠራው ሥራ የትብብር ፕሮጀክቱ የራሱን ሚና የሚጫወት እንደሆነም ዋና ተመራማሪው አውስተዋል፡፡  

በኢትዮጵያ ውስጥ እንሰት ለምግብነት የሚውለው በዋናነት በደቡብና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ነው ያሉት ዶ/ር ሳቡራ ተክሉ ለምግብነት በማይታወቅባቸው ሌሎች አካባቢዎች (ሰሜን ኢትዮጵያ) ለሚገኙ አርሶ አደሮች ስለእንሰት አመራረትና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ከመጠቀም አኳያ ያላቸውን ግንዛቤ ዳሰሳ ጥናት በማድረግ የእንሰት አመራረትና ድኅረ ምርት ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ ሌላኛው የፕሮጀክቱ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ሂደት ለተጠቃሚዎች ሥልጠና መስጠትን ጨምሮ አንድ የእንሰት ማቀነባበሪያ ማዕከል የሚቋቋም ሲሆን ይህም እንሰት ባልተለመደባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ተክሉን ከማስተዋወቅ አንጻር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም እንሰት የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ምግብ እንዲሆን እንደ ዩኒቨርሲቲ ዕቅድ መኖሩን ጠቅሰው የዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ የትብብር ፕሮጀክቶች ተክሉ ከኢትዮጵያ አልፎ በሌሎች ሀገራት ጭምር እንዲታወቅና ለምግብነት እንዲውል የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል፡፡ የእንሰት ድኅረ ምርት ሂደት ላይ ያሉ ችግሮችን የሚቀርፉ በርካታ ሥራዎች በዩኒቨርሲቲው እየተሠሩ ይገኛሉ ያሉት ዶ/ር ተስፋዬ የእንሰት ምርትን በሀገር ደረጃና በምሥራቅ አፍሪካ ለማስፋፋትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም በሽታን በመከላከል ላይ የሚሠራ ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ በመስኩ ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውነውን ሥራ ሙሉ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ መሰል ቀጠናዊ የትብብር ሥራዎች በሀገራቱ መካከል የሚኖረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከማጠናከር አንጻርም የጎላ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

እስከ አሁን ባለው የፕሮጀክቱ የሥራ ሂደት በቤተ ሙከራ ውስጥ ለሚሠሩ ሥራዎች ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን ለምግብነት የሚውሉና የማይውሉ የተለያዩ የእንሰት ዝርያዎች ተሰብስበው በኢትዮጵያ የምርምር ጣቢያዎች (Experimental Sites) እና በኬንያ በሚገኘው የምርምር ጣቢያ (Greenhouse) ውስጥ ለጥናት የሚውሉ ግብዓቶችን የማዘጋጀት ሥራ  እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አንድ የ2ና አንድ የ3 ዲግሪ ተማሪዎች እንዲሁም ከጆሞ ኬንያታ ዩኒቨርሲቲ ሁለት የ2ና ሁለት የ3 ዲግሪ ተማሪዎች የምርምር ሥራቸውን እንሰት ላይ እንዲያከናውኑና በዚህም ከፕሮጀክቱ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል ዕድል እንደተመቻቸላቸው ተመላክቷል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ሳቡራ ሻራ በዚሁ ፕሮጀክት ሥራ ላይ በኬንያ በነበራቸው ቆይታ የተመለከቷቸውን አዳዲስ ልምዶች ለተሳታፊዎች ያቀረቡ ሲሆን የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በተመራማሪው የቀረቡ ተሞክሮዎች እንደ ዩኒቨርሲቲ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገቡ ጠቃሚ ልምዶች እንደሆኑ አመላክተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በእንሰት ቅድመ ምርትና ምርት ሂደት እንዲሁም ምርታማነት መጨመር ላይ አተኩሮ የሚሠራ መሆኑ የሚበረታታ እንደሆነም የውይይቱ ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የግብርናና የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኖች፣ ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው የምርምር ማዕከላት ዳይሬክተሮችና የፕሮጀክቱ አባላት ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት