Print

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ‹‹ዝክረ ዐድዋ ድል ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ሰላም›› በሚል ርእስ 128ውን የዐድዋ ድል በዓል የካቲት 23/2016 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አክብሯል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብሔረሰቦች ም/ቤት ም/አፈ ጉባኤና የክልሉ ፕሬዝደንት ተወካይ አቶ ዳርጌ ዳሼ ዐድዋ ድል ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ከመላው ኢትዮጵያ ዳር እስከ ዳር በላቀ የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ወኔና ጀግንነት በመሰባሰብ በተባበረ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የጣልያንን ወራሪ ኃይል ድል በማድረግ ለዘመናት የማይደበዝዝ ዘላለማዊ ክብር እና ኩራት ያጎናጸፉን የአሸናፊነት የጋራ አኩሪ ታሪካችን ነው ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ዳርጌ የዐድዋ ድል ለመላው ኢትዮጵያዊያን የአሸናፊነትና የፅናት ተምሳሌት በመሆኑ የዛሬው ትውልድም ለአርበኞች ክብር እየሰጠን ከቀደመው ትውልድ አንሰን የታሪክ ተወቃሽ እንዳንሆን የጋራ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ድል በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን የማስረከብ ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን፡፡

የክልሉ ሕዝብ ም/ቤት ዋና አፈ ጉባኤና የዕለቱ የክብር እንግዳ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ በበኩላቸው ዐድዋ ኢትዮጵያዊያንን በብዙ ያስተሳሰረ አኩሪ ታሪክ መሆኑን ጠቅሰው ምንም እንኳ ውስጣዊ የአንድነት ፈተናዎች ቢገጥሙንም ሀገራዊ ህልውናችንን ሊፈታተን የሚመጣውን ጠላት አሳፍሮ የመመለስ አኩሪ ታሪክ እንዳለን ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ፀሐይ ውስጣዊ ጉዳያችንን በንግግር፣ በውይይትና በድርድር እየፈታን አብሮነታችንንና ሰላማዊ ግንኙነታችንን በማጠናከር ድህነትን ድል ነሥተን ዳግም ዐድዋን ማስመዝገብ ይገባናል ብለዋል፡፡

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ዱባለ የዐድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደምና አጥንቱን የገበረበት መሆኑን አስታውሰው ለአሁኑ ትውልድ አብሮነትን፣ ኅብረትን፣ መደማመጥንና በጋራ መቆምን የሚያስተምር በመሆኑ በሃይማኖት፣ በባህልና በቋንቋ ሳንለያይ በጋራ አጀንዳዎች ዙሪያ ያለንን መልካም እሴት ጠብቀን በመቆየት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥትና ለሰላም ግንባታ ልንጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዐድዋ ጦርነት የጣሊያን መንግሥትና ጦር በታጠቀው መሣሪያና ቴክኖሎጂ ቢመካም የዚያ ዘመን አውሮፓዊ ቅኝ ገዢ ኃይሎችን ድንጋጤ ውስጥ የከተታቸውና የውርደት ካባ ያከናነባቸው ድል በጀግኖች ኢትዮጵያውያን መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ የዐድዋ ድል የጣልያን መንግሥት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት የመያዝ ህልሙን ያከሰመ ታላቅ ብሔራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው የዐድዋ እሴቶችን ለመጠቀም ቃል መግባት ከዛሬው ትውልድ የሚጠበቅ ሰብእና መሆኑን ተናግረው የሕዝቦች እኩልነት፣ ነፃነት፣ ፍትሕና ግፍን የመታገል ነበልባል በትውልዱ ሁሉ ደምቆ እንዲወጣ የማድረግ ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡ ዐድዋ ለሌሎች ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌትነቱ እጅግ ታላቅ መሆኑን ያነሱት ተ/ፕ በኃይሉ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭቆናን የመቃወም፣ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና ክብርን የማስመለስ ዕድልን እንደሚወክል ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና የታሪክና ሥነ ሰብዕ ተመራማሪ ዶ/ር መሰለ ተሬቻ ‹‹ዝክረ ዐድዋ ድል ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና ሰላም›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ቁልፍ መልእክት ጣሊያን በዐድዋ ላይ እንደተሸነፈች እንግሊዞች በምዕራብ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ለመወሰን፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ቅራኔ በመፍጠር ምኒልክን ወጥሮ ለመያዝና የሐሰት ትርክቶችን ለመንዛት አቅደው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ለማሳካት ኦውግስቶስ ዋይሊድ የተባለ ሱዳናዊ ወደ ኢትዮጰያ በማስገባት የኢትዮጵያን ታሪክ እያበላሸ እንዲጽፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ አክለውም ከ30 በላይ የእንግሊዝ ተጓዥ ነኝ የሚሉ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡና ስለኢትዮጵያ የተበላሹ ታሪኮችን እንዲጽፉ በማድረግ የውስጥ አንድነታችንን ለማላላት ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ አሜሪካም  ድርጊቱን እያጋነነች ለዛሬው የብሔር ፖለቲካ ዳርጎናል ያሉት ዶ/ር መሰለ ምሁራኖቻችን ይህንን ዐውቀው የሕግ አግባብ ለሚያስፈልገው በሕግ አግባብ ምላሽ መስጠት እንዲሁም ልዩነቶችን ተወያይቶ መፍታት ካልተቻለ የዐድዋ ድል እየተሸረሸረ መሄዱ አይቀርም ብለዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበር ተተኪ አርበኛ ተስፋዬ ገመዳ ቀደምት አባቶቻችን ሀገራችንን ለመውረር የመጣ ባዕድ ጠላታችንን ድል ሊያደርጉ የቻሉት በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሳ ሳይለያዩና ሳይከፋፈሉ በአንድነት ኢትዮጵያ ብለው በመነሳታቸው መሆኑን ተናግረው ወጣቱ ትውልድ ከቀደምት አባቶች የወረሰውን አደራ ተቀብሎ የታሪክ ተረካቢ ብቻ ሳይሆን የራሱንም ታሪክ የሚጽፍ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ት/ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ቦሻ ቦምቤ ‹‹የዐድዋ ድል ዘለቄታዊ ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ›› እና የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ት/ክፍል መምህር አቶ አባይ ወርቁ ‹‹የሀገር ግንባታ መሠረታዊያን፡- ሀገራዊ ማንነት፣ እሴትና ጥቅም ግንባታ›› በሚሉ ርእሶች ላይ የውይይት መነሻ ጽሑፎች አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ኢንፎክን የመጻሕፍትና የመረጃ ማዕከል እና ዜብራ ሰርከስ ቡድን አባላት ዐድዋን የሚዘክሩ የተለያዩ ሥነ ጽሑፎች፣ ተውኔቶችና መነባንቦች ቀርበዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው መምህራንና ካውንስል አባላት መካከል የመረብ ኳስ ግጥሚያ፣ የደም ልገሳ እና ‹‹ዐድዋን በጥበብ›› የተሰኘ የሥነ ጽሑፍ መርሃ ግብርም የአከባበሩ አካል ናቸው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት