የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንፎክን የመጻሕፍትና መረጃ ማዕከል የብዕር ጥበብ በተሰኘ ዓመታዊ የሥነ ጽሑፍ ቀን የተለያዩ ደራሲያንና ገጣሚያን በተገኙበት የካቲት 24/2016 ዓ/ም በተለያዩ ሥነ ጽሑፎች፣ ተውኔቶች፣ ወጎችና መነባንቦች የዐድዋን ድል ዘክሯል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዕለቱ የክብር እንግዳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና የታሪክና ሥነ ሰብእ ተመራማሪ ዶ/ር መሰለ ተሬቻ ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልእክት ተተኪ የኢትዮጵያ ተረካቢዎች በመሆናችሁ በአርበኝነነት መንፈስና በተቆርቋሪነት ከቀደምት አባቶች የተረከባችሁትን ታሪክ መጠበቅና የራሱን ታሪክ የሚጽፍ ትውልድ መሆን አለባችሁ ብለዋል፡፡ ከ1902 ዓ/ም ስምምነት ጀምሮ እንግሊዞች ኢትዮጵያ ላይ አድማ በመቀስቀስ የፖለቲካ መሪዎችን ለ100 ዓመታት በማስገደድ መቆየታቸውን ያስታወሱት ዶ/ር መሰለ የኢትዮጵያ ምሁራን በሴራ የተጻፉ ጽሑፎችን በጥንቃቄ አበጥረው ሳይለዩ በመጠቀማቸው ብሔራዊ አንድነታችን እየተናጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ታሪክን ሲያነቡ እንደወረደ ከመቀበል ይልቅ ተጠራጣሪ መሆን፣ በሚገባ መመርመርና ሀገራዊ ጥቅምና ፍላጎትን መጠበቅ እንደሚያስፈልግም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በፕሮግራሙ የተገኘው ገጣሚ ኤልያስ ሽታሁን የተለያዩ ግጥሞችን ያቀረበ ሲሆን በጥቅሉ ‹‹ሰው ሁኑ!›› በማለት ታዳሚያን በሕይወት የሚያጋጥሟቸውን ጉዳዮች በወቅቱ በመወሰን ሕይወታቸውን በጥበብና አስተውሎት እንዲመሩ መልእክት አስተላልፏል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንፎክን የመጻሕፍትና መረጃ ማዕከል ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ተማሪ መታገስ ኃይሉ እንደገለጸው ማዕከሉ ከተመሠረተ 16 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን መጻሕፍትን በሃምሳ ሣንቲም እያከራየ የተማሪዎችን የንባብ ክሂሎት እያበረታታ ይገኛል፡፡ ማዕከሉ የፍልስፍና ምሽት፣ ቶክ ሾውና የመሳሰሉ የመድረክ ሥራዎችን የሚሠራ ሲሆን ተማሪዎች ከትምህርት ባሻገር ሰፊውን ሕይወትና ሥነ ጽሑፍ እንደሚለማመዱ ተማሪ መታገስ ተናግሯል፡፡ የብዕር ጥበብ ፕሮግራም በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን የዘንድሮው መርሃ ግብር የዐድዋ ድልን በመዘከር መከናወኑን የገለጸው ተማሪ መታገስ ለአሁኑ ትውልድ የዐድዋ አርበኞችን ጥንካሬና አንድነት በማሳየት በተሻለ መልኩ አእምሯቸውን መቅረጽ ያስፈልጋል ብሏል፡፡

የማዕከሉ የቀድሞ አባል አቶ ቢንያም ጉልላት ማዕከሉ በተናጠልም ሆነ ከሌሎች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ካሉ ክበባት ጋር በመጣመር በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ተማሪዎችን ሊያገለግል ይገባል ብሏል፡፡ ትምህርታቸውን አጠናቀው የወጡ አባላትም ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችና ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች የሁለገብ መጻሕፍት ስጦታ በማሰባሰብ ለማዕከሉ በማበርከት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት