በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች የልማታዊ ቡድን ሥልጠና ፕሮግራም (DTTP) በአርባ ምንጭ ከተማ ውስጥ በመናኸሪያ ግቢ የተከናወኑ የንጹሕ መጠጥ ውኃ መስመር ዝርጋታና የመንገደኞች ጊዜያዊ ማረፊያ እንዲሁም በሴቻ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ግቢ የተገነባው አነስተኛ ለHIV/AIDS ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የቅድመ መከላከያና ማማከሪያ አገልግሎት መስጫ ማዕከል የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የካቲት 23/2016 ዓ/ም ለማኅበረሰቡ የማስተላለፍ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በመናኸሪያ ግቢ የተከናወኑት የውኃ መስመር ዝርጋታና የመንገደኞች ጊዜያዊ ማረፊያ 210 ሺህ ብር እና በሴቻ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ግቢ የተገነባው አነስተኛ ለHIV/AIDS ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የቅድመ መከላከያና ማማከሪያ አገልግሎት መስጫ ማዕከል 220 ሺህ ብር በአጠቃላይ 430 ሺህ ብር ያህል በሆነ ወጪ ፕሮጀክቶቹ በተማሪዎች መከናወናቸው ተገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ የልማታዊ ቡድን ሥልጠና ፕሮግራም/DTTP/ በ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች አስተባባሪነት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ በማሰባሰብ ለማኅበረሰቡ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንደሚያከናውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ተማሪዎቹ ከሥራ ላይ በመምጣታቸውና ከሰው ጋር የመግባባት ልምድ ያዳበሩ በመሆናቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ያሉ ችግሮችን በሚገባ የሚያውቁም ናቸው፡፡ በመሆኑም ችግሮቹን ለመቅረፍ ከተለያዩ አካላት ገንዘብ በማሰባሰብ ለሠሩት ሥራ አድናቆት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የኮሌጁ የኅብረተሰብ ጤና ተማሪዎች የማኅበረሰቡን ችግሮች የሚያቀሉ መሰል ተግባራትን ማከናወናቸውን አስታውሰው ተሞክሮው በምኅንድስና፣ ግብርና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ሌሎችም የትምህርት ዘርፎች መሻገር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ተማሪዎቹ በሠሩት ሥራ መደነቃቸውን ገልጸው በተለይ በእጅ ንክኪ የሚተላለፉና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ከመቀነስ አንጻር እንዲሁም የማኅበረሰቡ ጤና እንዲጠበቅ ከማድረግ አኳያ መሰል በጎ ተግባራትን በሕዝባዊ ስፍራዎች ማበራከት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኅብረተሰብ ጤና ት/ቤት ዲን ረ/ፕ ስንታየሁ አበበ ተማሪዎች በልማታዊ ቡድን ሥልጠና ፕሮግራም በዋናነት የኅብረተሰቡን ችግሮች በመመርመር፣ በመለየትና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ቅድሚያ በመስጠት መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራሙ በተለይ በትምህርት ክፍሉ ካሉት ስድስት ፕሮግራሞች ጋር በማቀናጀት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማካተት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል ትኩረት ያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኅብረተሰብ ጤና ት/ክፍል ኃላፊ ረ/ፕ ሙስጠፋ ግላኝ በትምህርት ክፍሉ የልማታዊ ቡድን ሥልጠና ፕሮግራም ዋና ዓላማ የ2ኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር ማኅበረሰቡ ውስጥ ገብተው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመለየት በሚችሉት አቅም ለማኅበረሰቡ ችግር መፍትሔ መስጠት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የጋሞ ዞን፣ የጋሞ ልማት ማኅበር፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤት፣ የሴቻ ጤና አጠባበቅ ጣቢያና የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት አመራሮች፣ የከተማው ጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የብሎኬትና ሲሚንቶ አቅራቢ ድርጅቶች፣ ባለሆቴሎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት