የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት ከአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት እና ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያያ ማዕከል /ELIC- English Language Improvement center/ ጋር በመተባበር በ Communicative English የአንደኛ መንፈቀ ዓመት ውጤታቸው C- እና ከዚያ በታች ለሆኑ 372 የ1ኛ ዓመት ተማሪዎች ከመጋቢት 13-15/2011 ዓ/ም በተግባቦት ክሂሎት ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ እንደገለፁት በስልጠናው የተካተቱት የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋን በመረዳትና በመጠቀም ረገድ ከፍተኛ ክፍተት የሚስተዋልባቸው ከመሆኑም ባሻገር የእንግሊዝኛ ቋንቋ ውጤታቸውም ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም የንግግር ክሂሎታቸውን በማሻሻል እርስ በእርሳቸው በቋንቋው እንዲግባቡ፣ በሚያነቡበት ጊዜ በራስ መተማመናቸው እንዲጨምርና የሚማሩትን ትምህርት በቀላሉ እንዲረዱ ለማብቃት ስልጠናው ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

አቶ አንለይ አክለውም በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች አስቀድሞ ፈተና በመስጠትና ከ50 በታች የሚያመጡ ተማሪዎችን በተከታታይ በመደገፍ ትክክለኛ የሆነ ለውጥ የሚያመጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

አንድ ሰው ቋንቋ ተማረ የሚባለው ሰዋሰውን ተጠቅሞ ሀሳቡን መግለፅ ሲችል ነው ያሉት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማዕከል /ELIC/ አስተባባሪ መ/ር አብዱሰላም ቱርኬ ስልጠናው በተለይም በአንደኛ መንፈቀ ዓመት FX ያመጡ ተማሪዎች ለሚወስዱት የማሻሻያ ፈተና እና በቀጣይ ለሚማሩት ኮርስ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ የተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ውጤት በአብዛኛው ዝቅተኛ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ተከታታይነት ያለው ስልጠና ቢያዘጋጅ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡

ስልጠናው የተማሪዎችን የመናገር፣ የመፃፍና የማንበብ ክሂሎት በማሻሻል፣ በሰዋሰውና በሥርአተ ነጥቦች አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በስልጠናው 18 የእንግሊዝኛ ቋንቋ መ/ራን በአሰልጣኝነት የተሳተፉ ሲሆን የግል፣ የጥንድና የቡድን ሥራ እንዲሁም የእርስ በእርስ ውይይትና በመጨረሻ ላይም ግብረ መልስ አሰጣጥ ያካተተ ነበር፡፡

ሰልጣኝ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው የመግባባት ክሂሎታቸውን ከፍ የሚያደርግላቸው ከመሆኑም በላይ ለሚማሩት ትምህርት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት