ለቢዝነስና ልማት ፕሬዝደንትነት ተደርጎ በነበረው ግልፅ ውድድር ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን የጽ/ቤቱ ም/ፕሬዝደንት ሆነው መሾማቸውን የዩኒቨርሲቲው ቦርድ መጋቢት 9/2011 ዓ/ም በፃፈው ደብዳቤ  አሳውቋል፡፡

ወ/ሮ ታሪኳ ውልደትና እድገታቸው በሀዋሳ ከተማ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸራል ዲዛይን ቴክኖሎጂ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት አግኝተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በከተማ ፕላንና ማኔጅመንት ዲፕሎማ ያላቸው ሲሆን በአመራርነትና በሌሎች ዘርፎች በርካታ አጫጭር ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ ወ/ሮ ታሪኳ ከ2001 ዓ/ም ጀምሮ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ተቀጥረው እያገለገሉ የቆዩ ሲሆን ከትምህርት ክፍል ኃላፊነት ጀምሮ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ም/ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆን በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ ላለፉት ዘጠኝ ወራትም የቀድሞ የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ራሄል ኤልያስ ለትምህርት ውጪ አገር በመሄዳቸው ተወካይ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ወ/ሮ ታሪኳ ሹመታቸውን በማስመለከት በሰጡት ቃለ-መጠይቅ የተሰጣቸው ኃላፊነት ትልቅና ከባድ መሆኑን አስታውሰው በስራቸው የሚገኙትን የግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ የሥራ ፈጠራ ማበልፀጊያ፣ የገቢ ማመንጫ ዳይሬክቶሬትና ኢንተርፕራይዞችን ውጤታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡ በተለይ በውክልና በቆዩባቸው ዘጠኝ ወራት የየዘርፉን ጠንካራና ደካማ ጎኖች የዳሰሳ ጥናት በማድረግ መለየት መቻላቸውንና በዚህም መሠረት የተለያዩ ማስተካከያዎችን እንደሚያደረጉም ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከሚያስገነባቸው ትልልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል ዋነኛ በሆነው የዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ዙሪያ ሀሳባቸውን የሰጡት ወ/ሮ ታሪኳ አሁን ላይ አንዳንድ ግለሰቦች የግንባታ ሥራው ቆሟል ሲሉ እንደሚሰማ ገልፀው ይህ መረጃ ትክክል እንዳልሆነና የግንባታውን ከፍተኛ ወጪ የሚሸፍነው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ እንዲሁም ሌሎች የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት የተቋቋመው ዩኒቨርሲቲዎች ገቢያቸውን በራሳቸው እያመነጩ ወጪያቸውን በራሳቸው እንዲሸፍኑና ከመንግሥት በጀት ጥገኝነት እንዲላቀቁ ለማስቻል እንደሆነ የገለፁት ወ/ሮ ታሪኳ በዚህ ረገድ በዩኒቨርሲቲው ሦስት የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመው በሥራ ላይ ቢሆኑም እስካሁን ባላቸው የሥራ እንቅስቃሴ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ትርፋማና ውጤታማ ሊሆኑ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ለኢንተርፕራይዞቹ ትክክለኛ፣ የተሟላና ሊያሠራ የሚችል መመሪያ አለመኖሩ እንዲሁም ኢንተርፕራይዞቹ 3 መሆናቸው ለአስተዳደርም ሆነ ለቁጥጥር አመቺ አለመሆኑ እንደ ችግር ተለይተዋል፡፡ በመሆኑም ከሌሎች መሰል ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ ተወስዶ 6 ማኑዋሎች ያሉት መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ሦስቱ ኢንተርፕራይዞች ‹‹አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ›› በሚል መጠሪያ በስሩ ሌሎች የንግድ ዘርፎችን አካቶ በአንድ ማኔጅመንት እንዲመራ ተደርጎ ይዋቀራልም ብለዋል፡፡

ኢንተርፕራይዙን ትርፋማና ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ዩኒቨርሲቲው ትልቅ የመነሻ ካፒታል ሊመደብለት እንደሚገባ ያሳሰቡት ም/ፕሬዝደንቷ ሌሎች በኢንተርፕራይዙ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጽ/ቤታቸው በቁርጠኝነት ይሠራል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው በራሱ የሚያመነጨውን ገቢ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ በማዕከል ደረጃ የሚሠራ ሥራ ብቻ በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ በሁሉም

ካምፓሶች የገቢ ማመንጫ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን ለመክፈት እንቀስቃሴ እየተደረገ መሆኑንና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችንም የገቢ ምንጭ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት