ዩኒቨርሲቲው ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ዘመናዊ የወጥና የምግብ ማብሰያ ማሽኖችን አስመጥቷል፡፡
የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ አየልኝ ጎታ እንደገለፁት የወጥና የምግብ ቤት ሠራተኞችን በጭስ ሊደርስ ከሚችል የጤና እክል ለመታደግ፣ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማላመድ፣ ለማገዶ የሚወጣውን አላስፈላጊ ወጪ ለማስቀረት እንዲሁም በማገዶ ምክንያት የሚጨፈጨፉ ደኖችን ለመከላከልና የተስተካከለ የአየር ንብረት እንዲኖር ለማስቻል ማሽኖቹ ተገዝተዋል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

ማሽኖቹ ለእንጀራ እና ወጥ ዝግጅት የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ቁጥር በመቀነስና ከአላስፈላጊ የጉልበት ድካም በመታደግ ፈጣንና ጥራት ያለው ሥራ ለመሥራት የሚያግዙ መሆናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የማሽኖቹ ውጤት እየታየ በቀጣይ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሁሉም ካምፓሶች ተግባራዊ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ይሠራል ብለዋል፡፡

የማሽኖቹ መምጣት አላስፈላጊ የሥራ ጫናን በማስቀረት ጊዜን የሚቆጥብና በጭስ ምክንያት ሊደርስ ከሚችል የጤና መታወክ የሚታደገን ነው ያሉት በውኃ ቴክኖሎጂና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች የተማሪዎች ምግብና ወጥ ቤት ሠራተኛ ወ/ሮ ዝናሽ አሉላ ዩኒቨርሲቲው ከማሽኖቹ ጋር በተያያዘ በቂ የአጠቃቀም ስልጠና በመስጠት የተሻለ ሊያሠራን ይገባል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከገዛቸው የምግብ ቤትና የወጥ ቤት መሣሪያዎች መካከል 8 የወጥ መወጥወጫ፣ 6 የሻይ ማፍያ፣ 6 የቁሌት ማብሰያ፣ 7 የሽንኩርትና የድንች መላጫ እንዲሁም የልብስ ማጠቢያ  ማሽኖች ይገኙበታል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለምግብና ወጥ ቤት አገልግሎት በዓመት ከ5000 ሜትር ኩብ በላይ የማገዶ ፍጆታ ይጠቀማል፡፡