በማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት እና በቤልጂየም Antwerp ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመከታተል ላይ በሚገኙት አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ አስተባባሪነት አሜሪካ አገር ኮሎራዶ ከሚገኘው ‹‹Denver Lions Club›› ጋር በመተባበር በአርባ ምንጭ ከተማ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ  180 ተማሪዎች፣ መምህራንና የከተማው ነዋሪዎች የዓይን ምርምራና የንባብ መነፅር ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለፁት የሕክምና አገልግሎት ያገኙ ተማሪዎች  ከኮሚዩኒቲ፣ ከጫሞና ከርሆቦት ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ሲሆን የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች የእይታ ቅድመ-ምርመራ በማድረግ ተሳትፈዋል፡፡ አገልግሎቱን ካገኙት መካከል በርካቶቹ ተማሪዎች ሲሆኑ ይህም በሚማሩበት ወቅት በእይታ ችግር ምክንያት ሲገጥማቸውየነበረን ተግዳሮት በመቅረፍ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል፡፡

የፕሮግራሙ አስተባባሪና የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ የክለቡ አባላት በነበራቸው ቆይታ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረው በቀጣይ ጊዜም ሌሎች ከፍተኛ የዓይን ስፔሻሊስት ሐኪሞችን በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ተመሳሳይ ሥራ ለማከናወን ቃል እንደገቡላቸውም ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱን ካገኙ ሰዎች መካከል 55 በመቶው ዕድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ሲሆኑ 56ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ የአገልግሎት ወጪው በገንዘብ ሲተመን ከ9 መቶ ሺ ብር በላይ እንደሆነ ማወቅ ተችሏል፡፡