የዩኒቨርሲቲው ‹‹SAM-UP›› Students academic Mission Upgrade /የተማሪዎች የትምህርት ተልዕኮ ማሻሻያ/ ክበብ በ2011 ዓ/ም በ1ኛ መንፈቀ ዓመት ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡

የክበቡ ሰብሳቢ ተማሪ ብሩክ ዮሃንስ እንደገለፀው የክበቡ ዓላማ ከኩረጃና ሱስ የፀዳ ማኅበረሰብን በማፍራት የተሻለና የተቀላጠፈ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲፈጠር ማገዝ፣ ተማሪዎች በጥሩ ውጤት እንዲመረቁ ማስቻል እና በራስ የሚተማመኑና ጥሩ ሥነ-ምግባር ያላቸው ተማሪዎችን ማፍራት ነው፡፡

ከክበቡ ዋና ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የማጠናከሪያ ትምህርት በእያንዳንዱ ምዕራፍ ማጠቃለያ ላይ ለሴቶች፣ ለአንደኛ ዓመትና ውጤታቸው ዝቅተኛ ለሆነ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ዓመት ላሉ ወንድ 4,020 እና ሴት 2,520 በድምሩ ለ6,540 ተማሪዎች በመምህራንና ተማሪዎች አማካኝነት ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የኮምፒውተር ቤተ-ሙከራዎች በተገቢው መንገድ አገልግሎት እንዲሰጡ ክትትል መደረጉን፣ በመምህራንና ተማሪዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በቀላሉ እንዲፈቱ መደረጉን እንዲሁም የተለያዩ የሶፍትዌር ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ተማሪ ብሩክ ገልጿል፡፡ ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግ 96 ወንድ እና  2 ሴት ተማሪዎች እንዲሁም 5 መምህራን መሳተፋቸውን ሰብሳቢው ተናግሯል፡፡

በአተገባበር ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን አስመልክቶ የማጠናከሪያ ትምርት በሚሰጥባቸው ክፍሎች ውስጥ የመብራት እጥረት መኖሩ፣ አብዛኛው ክፍሎች በመምህራን የሚያዙ መሆናቸው እንዲሁም ፕሪንተር እና የክበቡ ማኅተም አለመኖሩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በቀጣይ ዩኒቨርሲቲው በበጎ ፈቃደኝነት የሚንቀሳቀሱ ተማሪዎችን በተሻለ ሁኔታ እንዲሳተፉ በማበረታታት እና ክበቡን በተለያዩ ግብዓቶች በመደገፍ እንዲጠናከር የበኩሉን አስተዋፅኦ ይወጣ ዘንድ ሰብሳቢው ጠይቋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት