በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የመምህራን ልማት ረቂቅ መመሪያ ላይ ግንቦት 8/2011 ዓ/ም ክላስተራዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እንደገለጹት ረቂቅ መመሪያው የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሰጠው ኃላፊነት መሠረት የተዘጋጀ ሲሆን በረቂቅ መመሪያው ላይ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ውይይቶች ተደርገውበት አሁን ላይ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በክላስተር እየተወያዩበት ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ወጥ የሆነ መመሪያ ባለመኖሩ ምክንያት ሲፈጠሩ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ መመሪያው ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ እንደሚጠበቅና ከውይይቶቹ በኋላ ማስተካከያዎች ተካተው ተግባራዊ እንደሚደረጉ ዶ/ር የቻለ ተናግረዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

መመሪያውን ካዘጋጁት የኮሚቴ አባላት አንዱ የሆኑት የዩኒቨርሲቲው መምህር ዶ/ር ሐብታሙ እንድሪስ መመሪያውን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት ረቂቅ መመሪያው የተዘጋጀበት ዓላማ በመንግሥት የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ጊዜው የሚፈልገውንና የደረስንበትን የዕድገት ደረጃ መሠረት በማድረግ ወጥነት ያለው የመምህራን ልማት ሥርዓትን በመዘርጋት ተገቢው አካዳሚያዊ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ችሎታ እና አመለካከት ያላቸውን መምህራን በመሳብ፣ በማቆየትና በማትጋት የትምህርትና ሥልጠና፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ጥራትና ውጤታማነትን ማረጋገጥ ነው፡፡

በውይይቱ ላይ የወላይታ ሶዶ፣ ጂንካና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡