በማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ‹‹አንድ ቅዳሜን ለሕዝቤ›› በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ግንቦት 10/2011 ዓ/ም በአባያ ሐይቅ ላይ የእንቦጭ አረም ነቀላ አካሂደዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከዚህ ቀደም ‹‹አንድ ቅዳሜን ለሕዝቤ›› በሚል መሪ ቃል የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን አስታውስው የዛሬው የአረም ነቀላም የዚሁ መርሀ ግብር አካል ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ተክሉ ገለፃ የዛሬው ፕሮግራም የመጀመሪያ እንደመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም የበጎ አድራጎት፣ የሠላም ፎረምና የተማሪዎች ኅብረት አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችን፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችን ያሳተፈ ተመሳሳይ ፕሮግራም እንደሚኖርና በዚሁ መሪ ቃል ሌሎች የበጎ አድራጎት ሥራዎችም በቀጣይ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው አረሙ በሐይቁ ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳትና በምን ያህል መጠን አረሙ በሐይቆቹ ላይ እንደተስፋፋ ለማወቅና የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማመላከት የሚያግዝ የምርምር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውሰው የዛሬው ፕሮግራም ጅምር እንደሆነና በቀጣይ በስፋት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ አረሙን በዛላቂነት ለማጥፋት ዩኒቨርሲቲው በሣይንስና ቴክኖሎጂ የታገዙ ዘዴዎችን ለማመንጨትና ለመተግበር  እንደሚሠራም  ዶ/ር ዳምጠው ገልጸዋል፡፡

የዘርፉ ተመራማሪና የIUC ፕሮጀክት ኃላፊ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ አረሙ አሁን ላይ ጉዳት እያደረሰ የሚገኘው በሐይቁ ዳርቻና ረግረጋማ አካል ላይ መሆኑን ጠቁመው ይህም ሐይቁ ላይ ባለው ማዕበልና ነፋስ ምክንያት አረሙ ወደ ዳር እየተገፋ ስለሚወጣ ነው ብለዋል፡፡ የአረም ነቀላው የተደረገበት ቦታ ዋሎ ረግረግ (wetland) እንደሚባልና ይህም 570 ሄክታር የሚሸፍን ሲሆን ቦታው ሙሉ በሙሉ በአረሙ መሸፈኑን ዶ/ር ፋሲል ገልፀዋል፡፡

በሐይቁ ዳርቻ ላይ የሚገኘውን አረም ለማስወገድ የሰው ጉልበት መጠቀም አሁን ላይ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን የጠቆሙት ተመራማሪው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የጀመረው የበጎ አድራጎት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል፡፡ ሌሎች ተፍጥሮአዊ በሆነ መንገድ አረሙን ለመቆጣጠር የሚያግዙ ዘዴዎችን ለመጠቀም ያግዝ ዘንድ አረሙን የሚመገብ ጢንዚዛ አምጥቶ ለመሞከር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እተሠሩ መሆናቸውን ዶ/ር ፋሲል ጠቁመዋል፡፡

የነቀላ ፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት አረሙ በሐይቁ ላይ ያለበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን እንደታዘቡ ተናግረው የአካባቢውም ሆነ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አረሙን በማስወገድ ሂደት ውስጥ በስፋት ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት