በአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት 19ኛው ዓለም አቀፍ የውኃ ሀብት ልማት ዓውደ ጥናት ‹‹የዉኃ ሀብታችን ለጋራ ልማታችን ይውላል›› በሚል ርዕስ ከግንቦት 16-17/2011 ዓ/ም ለተከታታይ 2 ቀናት ተካሂዷል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የመስኖ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ሚካኤል መሃሪ በንግግራቸው በኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች ዙሪያ ያሉ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ እንደገለጹት በአገሪቱ ከ120 ቢሊዮን ሜ.ኩ በላይ የምድርና 40 ቢሊዮን ሜ.ኩ የከርሰ ምድር ውኃ እንዲሁም 12 የውሃ ተፋሰሶች  ሲኖሩ ይህም  5.75 ሚሊየን ሄክታር የሚደርስ መሬት በመስኖ ማልማት የሚያስችል አቅም አለው፡፡ በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥ እስካሁን 20 ከመቶ ብቻ በመልማት ላይ መሆኑንና ከዚህ  ውስጥም አብዛኛው በአነስተኛ መስኖ ደረጃ እንዳለ ዶ/ር ሚካኤል ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ የመስኖ ልማት ዘርፍን ከማዘመን አንጻር ግልጽና ወቅታዊ ጥናት፣ ዲዛይንና የመረጃ ሥርዓት በመዘርጋትና አገር በቀል አቅም በማሳደግ የፋይናንስ አቅርቦት ማሻሻል፣ ግልጽ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መንደፍና ማስቀመጥ የሚያስችሉ ተግባራት እንዲሁም በሂደቱ በዘመናዊ መስኖ ከ120 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከማልማት ባለፈ በዘርፉ አዲስ ለሚመረቁ ከ30 ሺ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ማቀዱን አስገንዝበዋል፡፡

የውኃ ሃብትን ለመስኖ ልማት በአግባቡ መጠቀምና ህዝቡን ከመመገብ አልፎ ለውጭ ገበያ ከማዋል እና ለኢንደስትሪው ጥሬ እቃ ከማቅረብ አኳያ ብዙ መሠራት እንዳለበት ያወሱት ኮሚሽነሩ በቀጣይ ለአገራዊ እድገቱ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ተደርገው የሚሠሩ የመስኖ፣ የመጠጥ ውኃ እና ሌሎችም ፕሮጀክቶች በምርምር የታገዙ እንዲሆኑ መሰል ዓውደ ጥናቶች አስፈላጊ መሆናቸውንና መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በውኃ ሀብት ልማት ዘርፍ ተመራማሪዎችን፣ መምህራንን፣ ተማሪዎችን፣ በውኃ መስክ የተሰማሩ የልማት አጋሮችን እና ውሳኔ ሰጪ አካላትን በጋራ በማገናኘት የሀሳብና የልምድ ልውውጥ እንዲኖርና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል ግንኙነት ለመፍጠር እንዲሁም ውኃን ለዘላቂ ልማት መጠቀም በሚያስችሉ ጉዳዮችና  አግቦቦች ላይ ለመምከር አውደ ጥናቱ መዘጋጀቱን በዩኒቨርሲቲው የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል ገልፀዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በአፍሪካ ደረጀ በውኃው መስክ የልህቀት ማዕከል እንደመሆኑ በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት፣ ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ ብሎም በሌሎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች የአገሪቱን እምቅ የውኃ ሀብት በማሳደግና በመጠቀም ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ለማዋል እየሠራ እንደሚገኝ ዶ/ር አብደላ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ህይወትን ለማቆየት ከሚያስፈልጉ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል ውኃ ቀዳሚ ሲሆን በተለይ ውኃን ለመጠጥና ለተለያዩ ግልጋሎቶች ከመጠቀም ባለፈ ለግብርናና ለኢንደስትሪ እድገት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን የውኃ ሀብት እጥረትና የጥራት ጉድለት የሚስተዋል መሆኑን ፕሬዝደንቱ አውስተው የውኃ መጠን እየቀነሰ መምጣትና የጥራት ጉድለቱ ለማኅበራዊ ምጣኔ ሀብት ዕድገትና ለሥነ-ምህዳር ሥራዎች አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ የውኃ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ምርምር ማዕከል ጥናት አቅራቢ አቶ ለማ ተክሌ ቀደም ሲል ዝናብን ብቻ ጠብቆ የሚገኘው  ምርት በፍጥነት እያደገ ያለውን የህዝብ ቁጥር መመገብ ስለማይችል በዝናብ አጠር ቦታዎች ላይ ብቻ ሲሠራ የቆየውን የመስኖ ሥራ በሁሉም ቦታ በመጠቀም ህዝቡን የሀብቱ ተጋሪ እንዲሆን ማስቻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ተቋማቸው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሲደርቅ የነበረውን የወንዝ፣ የኩሬና የሐይቆችን ውኃ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ምርምሮች እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛዋ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጥናት አቅራቢ ወ/ሪት ምንታምር ፈረደ የጉድጓድ ውኃን ጥራት በመከታተልና ደረጃውን በማሻሻል ለመስኖ ልማት በማዋል ዙሪያ በአካባቢው በሚገኝ የወንዝ ገባሮችና ተፋሰሶች ላይ ያደረጉትን ጥናት ግኝት አቅርበዋል፡፡ በዚህም በከፍተኛ ዝናብ ወቅት፣ በዝቅተኛ እና በደረቅ ወቅት ሊኖር የሚችለውን የውኃ መጠን ለማወቅ ዓለም አቀፍ ሂደቶችን የተከተሉ የተለያዩ አመላካች ጉዳዮች ታሳቢ በማድረግ በየጊዜው ክትትል በማድረግና መረጃ ወስዶ በመገምገም ለዘላቂ ጥቅም ለማዋል የሚያግዝ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት እንዲሁም ከተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት በመጡ ምሁራን በሃይድሮሎጂና ቅንጅታዊ የውኃ አስተዳደር ልማት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በውኃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን፣ በተለዋዋጭ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም በውኃ ሀብት ልማት እየታዩ ባሉ ተግዳሮቶች ላይ ያተኮሩ ከ25 በላይ ጥናትና ምርምሮች በመድረክና በፖስተር መልክ ቀርበው በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የአዘጋጁ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የአዲስ አበባ፣ ሐረማያ፣ ባህርዳር፣  እና ደብረ  ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች፣ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የመስኖ ልማት ኮሚሽን እና የውኃ ሀብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም፣ የአማራ ዲዛይን እና ቁጥጥር ሥራ ኢንተርፕራይዝ፣ የአማራ ምርምር ማዕከል፣ የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ማዕከል፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢና ልማት ጥናት ማዕከል፣ የኦስትሪያው ኢንስብረክ ዩኒቨርሰቲ (University of Innsbruck, Austria) እና ሜክሲኮ የሚገኘው ባጃ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ (Autonomous University of Baja California, Mexicali)ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት