በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን እና የአሁን ማኅበረሰብ የውይይትና የምክክር መድረክ ለሦስተኛ ጊዜ በዋናው ግቢ መሰብሰቢያ አዳራሽ ግንቦት 18/2011 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡
የፕሮግራሙ ዓላማ የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበርን ለማጠናከር በሚረዳ መልኩ ውይይት በማድረግ ምሩቃኑ በዘላቂነት ከተቋሙ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማስፋት ዩኒቨርሲቲው የተቋቋመበትን ዋነኛ ዓላማ ለማስፈፀም የበኩላቸውን ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ነው፡፡ የቀድሞ ምሩቃኑ በተማሩበት ተቋም በመገኘት እርስ በእርስ እና ከቀድሞ መምህራኖቻቸው ጋር ትዝታዎቻቸውን እንዲያወጉ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም አሁን በተቋሙ ካሉ ተማሪዎች ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲፈጥሩ  በማድረግ ልምድ የሚያገኙበት መድረክ እንዲሆን ታስቦ ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዘ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳወሱት ምሩቃኑ ለዩኒቨርሲቲው አምባሳደር በመሆን በመማር ላይ ያሉ ተማሪዎች የተግባር እገዛ በማድረግና በየዘርፉ ያካበቱትን ልምድ በማካፈል አቅም መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል፡፡ ተማሪዎችም ከምረቃ በኋላ ያላቸውን ግንኙነት ተጠቅመው የሥራ ዕድል የሚያገኙባቸው አጋጣሚዎችን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው ገልፀው ለዚህ ተግባር መሳካትም በዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ጠንካራ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምሩቃኑ ባሉበት ሆነው ከተቋሙ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር የአባሳደርነት ሚና በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በማማከር ተግባራት ላይ በጋራ እንዲሠሩ እንዲሁም ምሩቃኑ በሚገኙባቸው ኢንደስትሪዎችና ተቋማት የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ለተግባር ትምህርት በሚላኩበት ወቅት ድጋፍ በመስጠትና ያካበቱትን ልምድ በማጋራት የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠይቀዋል፡፡ በዚህ መልኩ በጋራ በመሥራት ከዩኒቨርሲቲው ባለፈ ለአገር ሁለንተናዊ እድገት አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚቻልም የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በፕሮግራሙ ከአልሙናይ ጋር ስለሚኖር ግንኙነት፣ ግንዛቤ መፍጠሪያ መንገዶች፣ በሂደቱ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች፣ ቀደም ሲል በተካሄዱ ሁለት መድረኮች በተነሱ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣይ መደረግ በሚገባቸው ተግባራት ላይ ያተኮረ ሰነድ በዩኒቨርሲቲው ሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ተባባሪ ሬጂስትራር ዶ/ር ሐብታሙ እንድሪስ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በጉባኤው ማጠናቀቂያ የአልሙናይ ማኅበር መቋቋምን ተከትሎ የማኅበሩን ሰብሳቢና ም/ሰብሳቢ ምርጫ ለማካሄድ በተሰጠው ድምጽ አቶ ኤርሚያስ ዓለሙ እና ወ/ሪት ሣልሳዊት ባይነሳኝ በሰብሳቢነትና በም/ሰብሳቢነት እንዲመሩ የተሰየሙ ሲሆን ተመራጮችም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት