ዩኒቨርሲቲው 4ኛውን የማኅበረሰብ ሳምንት ‹‹በተፈጠረው ዕድል ማኅበረሰቡን እናገልግል›› በሚል መሪ ቃል ከሰኔ 25-28/2011 ዓ/ም በድምቀት አክብሯል፡፡ በበዓሉ ደም ልገሳ፣ ችግኝ ተከላ፣ የአረጋውያን ቤት እድሳት የመሳሰሉ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ጨምሮ የፈጠራ ሥራዎች ዓውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት በአጫጭር ሥልጠናዎች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች   የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ በልዩ ልዩ ሙያ ዘርፎች በማማከር፣ ለአቅመ ደካሞች የህግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት እና በተፋሰስ ልማት ሥራዎች ረገድ በዩኒቨርሲቲው የተከናወኑ ተግባራት የሚያበረታቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ቴክኖሎጂን በማሸጋገርና የምርምር ውጤቶችን ወደ ፕሮጀክት በመቀየር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ከሚጠበቀው ደረጃ አንፃር ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው በሁሉም የትምህርት መስኮች የሚያስተምሩ መምህራን በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ለመሳተፍ እየታየ ያለው ተነሳሽነት የሚበረታታ ሲሆን በቴክኖሎጂ ሸግግርና የምርምር ውጤቶችን ቀምሮ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር ከፍ ባለ ደረጃ እንዲከናወን የዩኒቨርሲቲዉ አስተዳደር በሚቀጥሉት ጊዜያት ትኩረት የሚሰጥበት ጉዳይ ይሆናል ብለዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ እስከ አሁን ባለው ልምድ በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ብለዋል፡፡ ለመማር ማስተማር 75 በመቶ ለምርምር 25 በመቶ ከተሰጠው የጊዜ ድርሻ አንጻር ለማኅበረሰብ አገልግሎት የተተወ የጊዜ ድርሻ ባለመኖሩ ተቋማቱ ለማኅበረሰብ አገልግሎት ሠራተኞቻቸውን የሚያስገድዱበት ሥርዓት አለመኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡

ዶ/ር ስምዖን በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማኅበረሰብ አገልግሎት የሚሰጥበት ማዕቀፍ ባለመኖሩ ተግባሩ በተቋማቱ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ አገልግሎቱ በምን መልኩ ሊሰጥ እንደሚችልና እንደሚገባ የሚያሳይ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ወሳኝ በመሆኑ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ብለዋል፡፡ ከፍተኛ የት/ት ተቋማት የሥልጠና ፕሮግራሞች ከማስፋፋት ጎን ለጎን የማኅበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት አቅማቸውን ከአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ማኅበረሰብ ተኮር ጉዳዮች በጥናት በመለየትና የዕቅዳቸው አካል በማድረግ እንደ ዋና ተቋማዊ ተግባር አድርገው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደተናገሩት ለአካባቢው ሁለንተናዊ ዕድገትና ልማት በበጀት ዓመቱ በዘርፉ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ለማስተዋወቅና በተማሪዎችና መምህራን የተሠሩ የፈጠራ ሥራዎችን ለማቅረብ ፕሮግራሙ ተዘጋጅቷል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለው የማኅበረሰብ አገልግሎት አሰጣጥን አስመልክቶ አንዳንድ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ የሆነ ደንብና መመሪያ አውጥቶ ወደ ሥራ መግባቱና መምህራንና ተመራማሪዎች ማገልገል መጀመራቸው እንዲሁም ለዘርፉ የሚመደበው በጀት ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ መምጣቱ ከተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎች መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

በበዓሉ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን ደረጃ ሁለትን ያጠናቀቁ የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ተማሪዎች ምረቃ ሥነ-ሥርዓትን ጨምሮ ለተለያዩ ት/ቤቶችና የሕዝብ ቤተ-መፃህፍት የመፃህፍትና ቤተ-ሙከራ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የሥራ ክፍሎችም የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት