ዩኒቨርሲቲው ሐምሌ 01/2009 ዓ/ም ለ30ኛ ጊዜ በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት፣ በሣምንቱ መጨረሻና በርቀት ፕሮግራሞች ያስተማራቸውን 534 የድህረ ምረቃ እና 4,979 የቅድመ ምረቃ በድምሩ 5,513 ተማሪዎች አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 4,164ቱ ወንዶች ሲሆኑ 1,349ኙ ሴቶች ናቸው፡፡

 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርሲቲው በልዩ ልዩ የትምህርት መስኮች የ2009 ተመራቂዎችን ጨምሮ ከ43 ሺህ በላይ ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡ በአያሌ ጥረትና ብርቱ ውጤት ለስኬት ለበቁት ምሩቃን፣ ወላጆች፣ ቤተሰቦችና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የተሰማቸውን ደስታም ገልፀዋል፡፡

የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ማጠናከር የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን እንደሚያሳድግ የገለጹት ፕሬዝደንቱ ይህንን በማሳካት ረገድ ዩኒቨርሲቲው በ2ኛው የእድገትና ትራንፎርሜሽን ዘመን የድህረ-ምረቃ ተማሪዎችን መጠን ከአጠቃላይ ተማሪዎች 10 በመቶ ለማድረስ አቅዶ 6.81 ማድረስ ችሏል ብለዋል፡፡ በተማሪነት፣ በመምህርነትና በአመራር ቦታዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሠራ ሲሆን በሁሉም መርሃ ግብሮች የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ በቅድመ ምረቃ 31.2 በመቶ፣ በድህረ ምረቃ 9.8 በመቶ እንዲሁም በመምህርነት 11.4 በመቶ ላይ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትርና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ታገሰ ጫፎ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ምሩቃን የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችሁን ማጠናቀቃችሁ አንዱ ምዕራፍ ሲሆን የቀሰማችሁትን እውቀት በመተግበር ነባራዊውን ዓለም የምትቀላቀሉበት የሁለተኛው ምዕራፍ ጉዟችሁ ስኬታማ እንዲሆን ራዕይ፣ መልካም ሥነ-ምግባርና ታታሪነትን መሰነቅ ይገባችኋል›› ብለዋል፡፡

ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪ ካህሱ ገብረዮሐንስ 3.88፣ ከተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ ተማሪ ፍፁም ደጀኔ 3.95፣ ከጤና ሣይንስ ኮሌጅ ተማሪ ቢንያም ዳንኤል 3.99፣ ከግብርና ሣይንስ ኮሌጅ ተማሪ ተስፋ ሁሴን፣ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ  ተማሪ አበባው ተሾመ 3.97 እና ከማኅበራዊ ሣይንስ ኮሌጅ ተማሪ ላኮ ፑሊያ 3.92 በማምጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመዋል፡፡

ከኢንስቲትዩቱ፣ ከየኮሌጆችና ከት/ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎችም የሥርዓተ-ፆታ ዳይሬክቶሬት ሽልማት አበርክቷል፡፡ ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪ ኤልሻዳይ ሙሉ 3.64፣ ከተፈጥሮ ሣይንስ ኮሌጅ ተማሪ ዘቢባ ሁሴን 3.92፣ ከጤና ሣይንስ ኮሌጅ ተማሪ ሜሮን ኃይሉ 3.93፣ ከግብርና ሣይንስ ኮሌጅ ተማሪ እታበዝ አያዬ 3.78፣ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ተማሪ ገነት ተሾመ 3.64፣ ከማኅበራዊ ሣይንስ ኮሌጅ ተማሪ ፍላጎት ተፈራ 3.64፣ ከህግ ት/ቤት ተማሪ ኤልሳ ፋንታሁን 3.71 እና ከሥነ- ትምህርትና ሥነ- ባህሪ ት/ቤት ተማሪ ኑሃሚን የኔሰው 3.55 በማምጣት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

የነርሲንግ ትምህርት ክፍል ተማሪ ቢንያም ዳንኤልና የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ትምህርት ክፍል ተማሪ ተስፋ ሁሴን 3.99 የሆነ ተመሳሳይ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሁለቱ ተማሪዎች ያላቸውን አጠቃላይ የ ‘A+’ ውጤት እና የወሰዱትን ክሬዲት ሀወር አስልቶ ተማሪ ቢንያም ዳንኤል 3.99190282 ሲያመጣ ተማሪ ተስፋ ሁሴን 3.99305556 በማምጣት የ2009 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲውን ዋንጫ አንስቷል፡፡ የጤና ሣይንስ ኮሌጅ የነርሲንግ ትምህርት ክፍል ምሩቋ ተማሪ ሜሮን ኃይሉ 3.93 በማምጣት ከሴት ተመራቂዎች በአንደኛነት የወርቅ ሀብል ተሸልማለች፡፡