የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በስሩ ካሉ የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት “በተፈጠረው እድል ማህበረሰቡን እናገልግል” በሚል ርዕስ ሁለተኛውን የማህበረሰብ አገልግሎት ሣምንት ከሰኔ 27-30/2009 ዓ/ም በፓናል ውይይት፣ ዓውደ ርዕይና በሌሎች የተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ሲሠሩ ፍላጎትን በሚገባ በማወቅ፣ በቅንጅት፣ ተጽኖናና ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም ተገቢ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ አካባቢን ከመቀየር አልፎ ህዝብንና ሀገርን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ሲሉ የኢፌዲሪ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ሚኒስትር አቶ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል፡፡ ይህን ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ለሀገራችን ህዳሴ ጉዞ እውን መሆን ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲውና በባለድርሻ አካላት ቅንጅት በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ቀደም ሲል የተከናወኑ ሥራዎችን ለማስተዋወቅና የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ለመለየትና ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ገልፀዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት እንቅስቃሴ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ያከናወናቸውን ተግባራት ያካተተ ሪፖርት በዳይሬክቶሬቱ የልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ባለሙያ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በሪፖርቱ የ2ኛ ደረጃና መሠናዶ ት/ቤቶችን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች፣ በአርባ ምንጭ 1ኛ ደ/ት/ቤት የመማሪያ ብሎክ ግንባታ፣ የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች፣ የችግኝ ማፍላትና ሥርጭት፣ ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት፣ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን የማስተማር ስነ-ዘዴ ሥልጠና፣ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት፣ በኤች.አይ.ቪና ተያያዥ ጉዳዮች ስልጠናና ድጋፍ፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት፣ የማማከርና አጫጭር ስልጠናዎች እና ሌሎች በዳይሬክቶሬቱ ማስተባበሪያዎች አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ቀርበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የምርምር ማዕከላትን የመመስረትና የማጠናከር ሥራዎች እየሠራ ነው፡፡ ሀገራችን በእድገትና በህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ለመድረስ ካሰበችበት የስኬት ማማ እንድትደርስ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በተሻለ ሁኔታ በመሥራት በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ድርሻውን በላቀ መልኩ ይወጣልም ብለዋል፡፡

ከጋሞ ጎፋ፣ ከደቡብ ኦሞ ህዝቦች እና ከሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞኖች የመጡ የተለያዩ ኃላፊዎች በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎትና በሌሎችም ዘርፎች ሥራዎችን ከዞኖቹ ጋር በቅርበት በመሥራት ለሁለተኛ ጊዜ በዚህ መልኩ ማስቃኘቱ የሚያስመሰግን ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ከዚህ በተሻለ ሁኔታ አገልግሎቱን ለማስኬድ ከዞኖችና ከወረዳ ሴክተር መ/ቤቶች ጋር ተቀናጅቶ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግሮች በጋራ ለመለየትና ለመፍታት ትኩረት እንዲሰጥና የጋራ ግንዛቤ መድረኮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

በመምህራንና በተማሪዎች በሙከራ ላይ ያሉ እና ለማህበረሰቡ የቀረቡ የፈጠራ ውጤቶች እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት የተከናወኑ አበይት ተግባራት በአውደ-ርዕይ መልክ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ተጎብኝተዋል፡፡ በአውደ ርዕዩ ከ20 በላይ የፈጠራ ሥራዎች፣ በሀገሪቱ የተሠሩና እየተሠሩ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በናሙና ማሳያ እንዲሁም ለተለያየ የአየር ጸባይ የሚሆኑ የግንባታ ዲዛይኖች ለእይታ ቀርበዋል፡፡  በልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አማካኝነት በአካባቢ መልሶ ማልማትና አካባቢ ጥበቃ በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ በሚገኘው ተራራማ ሥፍራ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የመስክ ላይ ጉብኝትም በእንግዶችና በተሳታፊዎች ጉብኝት ተደርጓል፡፡

በማህበረሰብ አገልግሎት ሥር ከሚገኙ ከወዜና ከሻራ ቀበሌያት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት የምግብ ቤት ሠራተኞች በተግባር ተኮር የጎልማሶች ት/ት ዕድል ተጠቃሚ ሆነው በመደበኛ የትምህርት ዘርፍ ከ3ኛ ክፍል ወደ 4ኛ ክፍል የተሻገሩ ተማሪዎች በፕሮግራሙ ላይ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላትና መምህራንን ጨምሮ ከጋሞ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ እና ሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አስተዳደር ጽ/ቤቶች እንዲሁም በሦስቱ ዞኖች ከሚገኙ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡