‹‹ራዕይ ሰንቀናል፤ ለላቀ ድል ተነስተናል›› በሚል መሪ ቃል ዩኒቨርሲቲው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ጥቅምት 06/2010 ዓ.ም በድምቀት አክብሯል፡፡

‹‹ሀገርን ያህል ውድ ሀብትና የሉዓላዊነት መገለጫ ለማወደስ ከሰንደቅ ዓላማ ክብርና ፍቅር በላይ ጥሩ ማሳያ የሚኖር አይመስለኝም›› ያሉት የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንቱ ተወካይ ወ/ሮ ራሄል ኤልያስ በሀገራችን የዲሞክራሲ አስተሳሰብ ጭላንጭልና በቂ መረጃ መለዋወጫ ሳይኖር እንኳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ለሠንደቅ ዓላማቸው ክብርና ፍቅር ሲሉ መስዋዕትነት መክፈላቸውን አውስተዋል፡፡ በዓሉ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፍፁም እኩልነትና በፈቃዳቸው የመሠረቷት የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ማሳያ ምልክት በመሆኑ ዜጎች የፍቅር ተምሳሌት ለሆነው ሰንደቅ ዓላማቸው ልዩ ክብር በመስጠት ለህዳሴ ጉዞው የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ወ/ሮ ራሄል ተናግረዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ እንደተናገሩት የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለሁሉም ወገኖች ግልፅነት ለመፍጠርና ከግንዛቤ ማነስ ወይም ሆን ብለው ብዝሃነትን ለመናድ የሚንፀባረቁ አስተሳሰቦችን ወደ ትክክለኛ አመለካከት እንዲመጡ ለማድረግ በብሔራዊ ደረጃ ይከበራል፡፡

በበዓሉ የሰንደቅ ዓላማ ምንነት፣ ታሪካዊ ዳራ በኢትዮጵያ፣ ሊሰጠው የሚገባ ክብርና ሊተገበሩ የሚገባቸው ደንቦች ላይ ገለፃ የተደረገ ሲሆን የሰንደቅ ዓላማ አሰቃቀልና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር ሥነ-ሥርዓትም ተከናውኗል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የፀጥታና ደህንነት አካላትና የአስተዳደር ሠራተኞች በአከባበር ሥነ- ሥርዓቱ ተገኝተዋል፡፡