77ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል ሚያዝያ 27/2010 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ተከብሯል፡፡ በዓሉ የኢትዮጵያ አርበኞች በወራሪው ፋሽስት ኢጣልያን ላይ የተቀዳጁትን ድል በመዘከር ለአሁኑ ወጣት የአገሩን ታሪክ እንዲያውቅና በተሰማራበት መስክ ስኬታማ ለመሆን ወኔ እንዲሰንቅ የሚያሳስብ ነው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ህልውና ያደረጉት አኩሪ ተጋድሎና መስዋዕትነት ከቶ ሊዘነጋ የማይችል ታሪክ ነው ብለዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድም የአገራችንን እድገትና ብልጽግና ወደ ኋላ የሚጎትቱ ችግሮችን ልክ እንደ አባት አርበኞቻችን በአንድ ሀገራዊ ስሜት ድል ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የማህበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን አቶ ሙሉጌታ ደበሌ እንደተናገሩት የድል በዓልን የምናከብረው በባርነት ሊገዛን ታጥቆ የመጣውን የፋሽስት ኢጣሊያን ጦር ድል ነስተው የአገራችን ሉዓላዊነት ተከብሮና ነጻነታችን ተጠብቆ እንድንኖር ያደረጉንን ጀግኖች አባቶቻችንን ለመዘከር ነው፡፡ እኛም ልክ እንደ አባቶቻችን ሁሉ የጊዜያችን ጠላት የሆነውን ድህነትን   በጀግንነት ታግለን የበለጸገች ኢትዮጵያን ልንፈጥር ይገባል ብለዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የታሪክ ተመራማሪ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃይለማሪያም በበኩላቸው አዲሱ ትውልድ በታሪኩና በማንነቱ እንዳይሸማቀቅ፣ ዛሬን በሙሉ ልብ ለመጋፈጥና ነገንም አርቆ ለማየት እንዳይፈራ እና አባቶቻችን  በደማቸው ያቆሟትን ሀገር ለመጠበቅና እድገቷን ለማፋጠን ከወዲሁ አዲስ ራዕይ እንዲኖረው አሳስበዋል፡፡

በ1888 ዓ.ም የአድዋ ድል የተበሰረበትንና ከ1928-1933 ዓ.ም ድረስ ያለውን ሁለተኛውን የኢጣሊያን ወረራ ጊዜ የታሪክ ጸሐፊዎች የጻፏቸውን እውነታዎችና በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ ሴት አርበኞች የተጫወቱትን ሚና የሚያወሱ ጽሑፎችን የታሪክ መምህራን አቅርበዋል፡፡

የፋሽስት ኢጣልያ ጦር የ1888ን ሽንፈት ለመበቀል ከ40 ዓመት በኋላ በ1928 ዓ.ም እንደገና ስትነሳ ሀገራቸውን በጠላት እጅ ላለመጣል የኢትዮጵያ አርበኞች በዱር በገደሉ ተዋድቀዉ ያስገኙልንን ነጻነትና ያስረከቡንን ሉዓላዊት ሀገር የእነሱን የጀግንነት መንፈስ ተላብሰን እድገቷን በሥራችን ልናቀና እንደሚገባን የታሪክና የቅርስ አጠባበቅ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ካሱ ጡሚሶ ጠቁመዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከጋሞ ጎፋ ዞን የመጡ 3 አባት አርበኞችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡