የዩኒቨርሲቲው ህግ ትምህርት ቤት ከደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ ጋር በመተባበር በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ልዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ 180 አቃቢያን ህጎችና መርማሪ ፖሊሶች በወንጀል ምርመራ ዘዴ፣ በክስ አመሰራረትና በክርክር ክህሎት፣ በህግ ማርቀቅ እና በህግ ምርምር መርሆችና አተገባበር ላይ ያተኮረ ስልጠና ከግንቦት 6-8/2010 ዓ/ም ለተከታታይ 3 ቀናት ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የስልጠናው ዓላማ የህግ ባለሙያዎችን የማስፈፀም አቅም በማሻሻልና የሙያ ክህሎትን በማሳደግ በፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ቁልፍ ችግር ሆኖ የሚታየውን የአቅም ውስንነትና የዕውቀት ክፍተት መሙላት እንዲሁም ብቁ አገልጋይ እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑን የደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ የህግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማስረፅ ሥራ ሂደት ም/ኃላፊ አቶ ጥላሁን አማኑኤል በመክፈቻ ንግግራቸው ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ጥላሁን ገለፃ የፍትህ ተቋም ዋነኛ ሥራ የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደመሆኑ መጠን ህግን በማስከበር ረገድ በየደረጃው ባሉ የፍትህ አካላት ተልዕኳቸውን በተገቢው መንገድ መረዳትና መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፍትህ ተቋማቱ የሰው ኃይልም የዜጎችን የህግ ግንዛቤ ለማዳበር፣ ሊደርስባቸው ከሚችለው ጥቃት ተጠብቀው ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩና ንብረታቸው እንዲጠበቅ ለመከላከል፣ በወንጀል ህጉ አጥፊውን በመለየትና ተገቢውን ፍርድ በመስጠት ዳግመኛ ወንጀል እንዳይሠራና ለሌሎችም ሆነ ለራሱ ትምህርት እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያስችል ሙያዊ ብቃት ሊኖረው ይገባል፡፡

ብዙውን ጊዜ የወንጀል ድርጊት የሚፈፀመው በስውር በመሆኑ ወንጀል ፈፃሚዎችን ከንፁሃን ለይቶ ሰብዓዊ መብታቸው ሳይነካ እንዲቀጡ ማድረግ ከፍተኛ የወንጀል ምርመራ፣ ክስ ዝግጅትና ክርክር ዕውቀትና ክህሎት የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ በየወቅቱ የሚሰጡ አጫጭር የሥራ ላይ ስልጠናዎች ብቃትን ከማሳደግ አኳያ ፋይዳቸው ከፍተኛ እንደሆነም አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡

ስልጣን ባለው አካል በወጣ ህግ አታድርግ ተብሎ የተከለከለውን ማድረግ ወይም አድርግ ተብሎ የታዘዘውን አለማድረግና ከግብረ-ገብ ውጪ የሆነ ድርጊት ወንጀል መሆኑን አሰልጣኝ የደቡብ ብ/ብ/ህ ክልላዊ መንግሥት አቃቢ ህግ አቶ ዓሊ ሰኢድ ገልፀዋል፡፡ ህጉም የራሱ የሆነ መርህ ያለውና የተከለከሉ ድርጊቶች፣ ህጉን ለማስከበርና ለማስፈፀም ኃላፊነት ያለባቸውን ተቋማት ኃላፊነትና ግዴታ እንዲሁም ወንጀሎች የሚያስከትሉትን ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎችን በዝርዝር አካቶ ያያዘ ነው ብለዋል፡፡

በስልጠናው ቆይታ የወንጀል ህግ ዓላማ፣ የወንጀል ምርምራ ዓላማና መርህ፣  የወንጀል ምርመራ ዓይነቶችና ዘዴዎች፣  ወንጀል ከተፈፀመ በኋላ የሚደረጉ የምርመራ ደረጃዎች፣ የወንጀል ምርመራ ዘዴዎች፣ የወንጀል ስፍራ ምንነት፣ የወንጀል ስፍራ ምርመራ፣ ማስረጃ አሰባሰብ፣ ቃል አቀባበልና ባህሪያቱ፣ ብርበራ፣ መበርበሪያ ትዕዛዝ፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መበርበር፣ በብርበራ የተያዙ ዕቃዎችና ማስረጃዎች አያያዝ፣ ተጠርጣሪ ሰው ስለመያዝና በዋስ ስለመልቀቅ፣ የወንጀል ምርመራ የሚቋረጥባቸው ምክንያቶች፣ በወንጀል ምርመራ መዝገብ ላይ አቃቢ ህግ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች፣ የህግ ምርምር መርሆዎችና አተገባበር እንዲሁም ህግ ማርቀቅን አስመልክቶ ዝርዝር ገለፃና ውይይት ተካሂዷል፡፡

የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት ሰልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ሳይሸራርፉ በተግባር ላይ ማዋል እንደሚጠበቅባቸውና የተሻለ፣ ቀልጣፋና ፈጣን  ብሎም ግልፀኝነት የሰፈነበት አሠራር እንዲቀጥል ወደየመጡበት የፍትህ ጽ/ቤትና የፖሊስ ተቋማት ሲሄዱ ያገኙትን የግንዛቤ ዕውቀት ለሌሎች ባለሙያዎች ማካፈል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ከፍትህ ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ የምርምር ተግባራት እንደሚከናውኑና የክህሎት ክፍተት ማሻሻያ ስልጠናዎች እንደሚዘጋጁ ጠቁመዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት በመረጃ አሰባሰብና በቃል አቀባበል እንዲሁም በሥራ ላይ ያሉ ክፍተቶችን እንዲለዩና በህግ ዙሪያ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያጎለበቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡