የዩኒቨርሲቲው ሥነ-ትምህርትና ሥነ - ባህሪ ሣይንስ ት/ቤት በመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህርነት ለሦስት ወራት ያሰለጠናቸውን 142 ሴት ዕጩ ርዕሳነ መምህራን ግንቦት 18/2010 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል:: ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የስልጠናውን የሦስት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የሥነ-ትምህርት ት/ት ክፍል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ሳጶ እንደገለፁት  የሴቶችን የአመራርነት ክህሎትና ብቃት በማሳደግ በ1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሴት አመራርነት ድርሻን ወደ 50 በመቶ ከፍ ለማድረግ መንግሥት የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ለዕጩ ርዕሳነ መምህራኑ ስልጠናው ተሰጥቷቸዋል፡፡ ስልጠናው 70 በመቶ በተግባር 30 በመቶ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የተከናወነ ሲሆን በፖሊሲ፣ በአመራርነት ሙያ እና በትምህርት ዘርፍ መካተት ያለባቸው አንኳር ጉዳዮችን ይዟል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ከሀገራችን የህዝብ ቁጥር መካከል ግማሽ ያህሉን የሚሆኑትን ሴቶች ያላሳተፈ ልማትና ዕደገት የማይታሰብ መሆኑን ገልፀው በተለይ በትምህርት ዘርፍ በአመራርነት የሚሰማሩ ሴቶች ለሌሎች ሴቶች አርአያ በመሆን ውጤታማ ሴት ተማሪዎችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው ሴቶች ከማህበራዊ ተጽዕኖዎች ተላቀው ወደ አመራርነት እንዲመጡ ማድረግ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲው አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰው የዛሬዎቹ ተመራቂዎችም መንግሥትና ህዝብ የጣለባቸውን አደራ በመገንዘብ ኢትዮጵያዊ ሥነ-ምግባር የተላበሱና ሀገራቸውን የሚወዱ ዜጎችን ለማፍራት ብሎም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የማይተካ የአመራርነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ አሳስበዋል፡፡

የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ ለሀገር እደገትም ሆነ ብልጽግና የሴቶች ተሳትፎና የአመራርነት ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረው ተመራቂዎች የነገይቱ ኢትዮጵያ ህልውና መሰረት የሆኑትን ት/ቤቶች በብቃት በመምራት ሴት ልጅ ዕድሉ ከተሰጣት ታሪክ መሥራት እንደምትችል በተግባር ማሳየት አለባችሁ ብለዋል፡፡

ከተመራቂዎች መካከል ከወላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ የመጡት መ/ርት ኢየሩሳሌም ስምዖን በአስተያየታቸው የትምህርት አመራሩ ብቃት ማነስ አንዱ የትምህርት ጥራት ማነቆ መሆኑን ገልፀው ተመራቂዎች በስልጠናው ያገኘነውን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም በአመራርነት ሚና መንግስትና ህዝብ የጣለብንን አደራ በብቃት መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ሌላዋ ተመራቂ ከጋሞ ጎፋ ዞን አ/ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የመጡት መ/ርት አስራት ንጉሴ በስልጠናው ለሥራቸው አጋዥ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ወደፊትም መሰል ስልጠናዎች ለሌሎች ሴቶች በመስጠት ወደ አመራርነት የማምጣቱ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ተመራቂዎች እና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ለተመራቂ ሰልጣኞች የምስክር ወረቀት በመስጠት ሥነ-ሥርዓቱ ተጠናቋል፡፡