የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ለኮሌጁ መምህራን በOpen Data Kit /ODK/ ሶፍትዌር ላይ ከግንቦት 10-11/2010 ዓ/ም ለ2 ተከታታይ ቀናት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ርት ኤደን ከበደ እንደገለፁት የስልጠናው ዓላማ መምህራን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከመማር ማስተማር ሥራቸው በተጓዳኝ የማህበረሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ውጣ ውረድ ያልበዛባቸው፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ጥራት ያላቸውና ውጤታማ ምርምሮችን እንዲያከናውኑ ማስቻል ነው፡፡

የኮምፒውተር ሣይንስ ትምህርት ክፍል መምህር አሰልጣኝ አልአዛር ባህሩ ሶፍትዌሩን አስመልክቶ ሲናገሩ odk በውስጡ የተለያዩ ማዕቀፎችን/ፓኬጆች/ የያዘ፣ የመረጃ መቆጣጠሪያ ያለው፣ መረጃዎችን በወረቀት የመሰብሰብ ዘዴን በማስቀረት ስማርት ስልኮችን እንዲሁም ታብሌቶችን በመጠቀም መረጃን መሰብሰብ የሚያስችልና የሰበሰቡትን መረጃ በማውጣት ለትንታኔ የሚጠቀሙበት ሶፍትዌር ነው ብለዋል፡፡ ሶፍትዌሩ ማንኛውም ሰው በነፃ ሊጠቀመው የሚችል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

መ/ር አልአዛር አክለውም ሶፍትዌሩን በመጠቀም የጥናትና ምርምር ሥራን ማከናወን የወረቀትና የማተሚያ ቀለም ወጪ እንዲሁም በህትመት ወቅት የሚፈጠረውን የአየር ብክለት ከመቀነሱም በተጨማሪ ሶፍትዌሩን በመጠቀም የተሰበሰበው መረጃ የተሻለ ጥራት እንዲኖረው ያስችላል ብለዋል፡፡ በመሆኑም መምህራን በቀጣይ ሶፍትዌሩን በመጠቀም ለማህበረሰቡ የሚጠቅም ምርምር ለመሥራት እንዲበረታቱ አሳስበዋል፡፡

ሰልጣኝ መምህራን በሰጡት አስተያየት ሶፍትዌሩ በወረቀት መረጃ የመሰብሰብ ሂደትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስና አስፈላጊውን መረጃ በቀላሉ ለማዋቀር የሚያገለግል በመሆኑ በቀጣይ ለሚያከናውኗቸው የምርምር ተግባራት መንገድ ከፋች ነው ብለዋል፡፡