አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ2011 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ቅበላና የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያጠናቀቀ መሆኑን ገለፀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት 6,148 በመደበኛ እንዲሁም ከ3,000 በላይ አዲስ ተማሪዎችን በርቀትና በተከታታይ ትምህርት ይቀበላል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እንደገለጹት ለተማሪዎች ቅበላ ያግዝ ዘንድ የመማሪያ ክፍሎች፣ የማደሪያ ዶርሞች እንዲሁም የውኃና የመብራት መስመሮችን የመጠገንና ምቹ የማድረግ ሥራዎች በሁሉም ኮሌጆችና ኢንስቲትዩቶች የዝግጅት ምዕራፍ ዕቅድ አካል ሆነው እየተተገበሩ ሲሆን የቤተ-መጽሐፍትና የቤተ-ሙከራዎች ግብአት ማሟላት ሥራም እየተሠራ ነው፡፡

 

በት/ት ዘመኑ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ለተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት አስፈላጊ ግብአቶችን ለማሟላት እና በተለይም ለመምህራን ልማት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ መምህራንን ለማሟላት የአዳዲስ መምህራን ቅጥር እየተፈፀመ ሲሆን የመምህራኑን የማስተማር አቅም ለማጎልበት መደበኛ እና አጫጭር ሥልጠናዎች እንደሚሰጡና ካለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ አዲስ የማበረታቻ ሥርዓት ጭምር በመዘርጋት የከፍተኛ ዲፕሎማ (HDP) ፕሮግራም ተጠናክሮ እንደሚሰጥ ም/ፕሬዝደንቱ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪ ለሴት፣ ለአካል ጉዳተኛ እና ልዩ ድጋፍ ከሚሹ አካባቢዎች ለሚመጡ ተማሪዎች የሚሰጥ የማጠናከሪያ ትምህርት እና ሌሎች ድጋፎች በዚህ ዓመትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት ዶ/ር የቻለ በዩኒቨርሲቲው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የመማር ማስተማር ሥራ ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን ከተማሪዎች ተወካዮችና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ የተማሪዎች የሥነ-ምግባር መጓደል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ፈተናና ችግር መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት በተለይ ከሱስ ጋር ተያይዞ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ለማስተካከል የተማሪዎች የባህሪ ተሃድሶ ማዕከል በማቋቋም ይሠራል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ ባሉ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ለሚሠሩ ሠራተኞች ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው የነፃ ትምህርት እድል እንደሚሰጥ የታወቀ ሲሆን በዚህ ዓመትም በተለይ ለጤናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት ለ15 የጤና ባለሙያዎች የነፃ ትምህርት ዕድል መስጠቱን ዶ/ር የቻለ ገልፀው ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት በአጠቃላይ 70 ሰዎች የዕድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ በአዲሱ የትምህርት ጥራት ፍኖተ ካርታ ዙሪያ የማኅበረሰብ ውይይት የሚያደርግ ሲሆን የነባርም ሆነ የአዲስ ገቢ ተማሪዎች ቅበላና ምዝገባ ጥቅምት መጀመሪያ ላይ እንደሚሆን ማወቅ ተችሏል፡፡