በክረምት መርሃ ግብር በተለያዩ ኢንደስትሪዎች በሥራ ላይ ልምምድ የቆዩ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራን ጥቅምት 06/2011 ዓ.ም የፋከልቲ ኃላፊዎች በተገኙበት የምልከታ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል እንደገለፁት መምህራኑ ለሥራ ላይ ልምምዱ የተላኩት በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የሚያስተምሩትን ትምህርት በተግባር እንዲያዩትና ከአዳዲስ አሠራሮች እንዲሁም ሶፍትዌሮች ጋር እንዲተዋወቁ ለማስቻል ነው፡፡

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ደርበው የሥራ ላይ ልምምዱ መምህራኑ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ያላቸውን ዕውቀት በተግባር ማየት እንዲችሉ ከማድረጉ ባሻገር ለተማሪዎቻቸው ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት ማካፈል እንዲችሉ ከማድረግ አኳያ ሚናው የጎላ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ መምህራኑ በሥራ ላይ ልምምዱ ወደ ተለያዩ በውሃው ዘርፍ የሚሠሩ ተቋማት የሄዱ ሲሆን በዚህም በርካታ ጠቃሚ ልምዶችን ከማግኘታቸው ባሻገር በተቋማቱ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የምርምር ርዕስ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ጭምር ማግኘት መቻላቸውን መምህራኑ ካቀረቡት ሪፖርት መረዳት ተችሏል ብለዋል፡፡

ለልምምዱ የሄዱ መምህራን በሰጡት አስታያየት የሥራ ላይ ልምምዱ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የሚያስተምሩትን ትምህርት በተግባር ማየት እንዲችሉ እንደረዳቸው ገልፀዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ ልምምዱ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ አሠራሮችና ሶፍትዌሮች ጋር እንዲተዋወቁ እንዳገዛቸው ገልፀው ይህም ለመማር ማስተማሩ ሥራ አጋዥ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ፕሮግራሙ ተጠናክሮ ቢቀጥል ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል፡፡