የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአሁንና የቀድሞ ማኅበረሰብ አዲስ አበባ በሚገኘው የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር አዳራሽ ኅዳር 16/2011 ዓ/ም ውይይት አካሂደዋል፡፡ የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች በሥራ ላይ በሚገኙ የዩኒቨርሲቲው ቀደምት ምሩቃን ነው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎችና ምሩቃን በልምድና በእዕውቀት ልውውጥ እንዲሁም በሌሎች መስኮች ማስተሳሰር፣ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ መምህራንና ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን በመማር ማስተማር ሂደት የሚደግፉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው እያሉ ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተወጡ በቀጣይ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ባለሙያና እንደ ዜጋ የሚታነፁባቸው ጉዳዮች በውይይቱ ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው፡፡

አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች ዩኒቨርሲቲው ጥራት ያላቸውን ተማሪዎች በማፍራት አንጋፋ መሆኑን አንስተው ይህንን ዝናውን ጠብቆ ለማቆየት በትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ አደራ ያሉ ሲሆን እነርሱም ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመቆም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የውይይቱ አዘጋጆች በዩኒቨርሲቲው የዕድሜ ዘመን አገልግሎት ላበረከቱ ሁለት መምህራን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ያለው ማህበረሰብ የቀድሞ ተማሪዎችን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ከገቡበት ጀምሮ ተመርቀው እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ከጎናቸው በመሆን ሲደግፍ መቆየቱንና አሁንም ተመሳሳይ ተግባር እያከናወነ መሆኑን በማውሳት ለአካባቢው ማህበረሰብ ተወካይ ሽማግሌዎች የምስጋናና የዕውቅና ስጦታ አበርክተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመዝጊያ ንግግራቸው ውይይቱ ውጤታማ መሆኑን ገልጸው  የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተሰጡ አስተያቶችን ለመተግበር ዩኒቨርሲቲው ተግቶ እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች በጎ አድራጎት ክበብን ለመደገፍ የገንዘብ መዋጮ የማሰባሰብ ሥራ የተሠራ ሲሆን በዚህም ስምንት መቶ ሺህ ብር ያህል ማሰባሰብ ተችሏል፡፡ በዕለቱ በቀድሞው የአርክቴክቸር ተመራቂ ትዕዛዙ ሲማ የተሰራ ዩኒቨርቲውን የሚገልፅ ምስል ለጨረታ ቀርቦ  በአንድ መቶ ሺህ ብር አቶ አብዲ ፈቃዱ አሻናፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቅ እና ከክበቡ መሥራቾች አንዱ የሆኑት አቶ አንዋር ሰኢድ አብዱራህማን ለቻሪቲ ክበብ  ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በየዓመቱ ሦስት መቶ ሺህ ብር ለመደገፍ ቃል ገብተዋል ፡፡
በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው የአሁንና የቀድሞ አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ መምህራንና ምሩቃን፣ የአርባ ምንጭ ከተማ የአገር ሽማገሌዎች፣ የአሁኑ የተማሪዎች ሕብረት፣ የበጎ አድራጎትና የሠላም ፎረም ተወካይ ተማሪዎች ታድመዋል፡፡