የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ዲኖች የሙያ ማበልፀጊያ ማዕከል በማቋቋም ዙሪያና በማዕከሉ ተግባራት ላይ ከEthiojob.net ከመጡ ባለሙያዎች ጋር ህዳር 4/2011 ዓ.ም ውይይት አድርገዋል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዴሊቨሮሎጂ ዩኒት አስተባባሪ ዶ/ር ጌታነህ ተስፋዬ እንደገለፁት ተማሪዎችን በቀለም  ትምህርቱ ከማብቃት ባሻገር  ለሥራው ዓለም ብቁ አድርጎ ማውጣት የዩኒቨርሲቲው ኃላፊነት እንደሆነ ተናግረው በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው የማበልፀጊያ ማዕከሉን በማዕከል ደረጃ ከማቋቋም ባሻገር በየካምፓሱ ባለሙያዎችን በመመደብ ተማሪዎች ገበያው በሚፈልገው ልክ ተፈላጊውን እውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
የEthiojob.net የዕጩ ሠራተኞች ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ኮከብ አየለ በበኩላቸው የሙያ ማዕክሉን አስፈላጊነት አስመልክተው ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ፣ ለመቀጠር ብቁ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር በህይወት ዘመናቸው ሁሉ ሙያቸውን ማጎልበት የሚችሉበትን መንገድ በማሳየት ረገድ የማይተካ ሚና ይጫወታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የEthiojob.net ሙያ ማበልፀጊያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ንፍታለም ቢኒያም እንደገለፁት ተማሪዎች ተመርቀው ከወጡ በኋላ የሥራ ላይ ክህሎት ማነስ እንደሚታይባቸውና ማዕከሉ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት የተለያዩ ሥልጠናዎችን  በመስጠት ለመቀጠር ብቁ እንዲሆኑ ማድረግን ዓለማው አድርጎ እንደሚቋቋም ገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ ሥራውን ከጀመረ 20 ዓመታትን እንዳስቆጠረ የተናገሩት አስተባባሪው ማዕከሉ አሁን ላይ በ10 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየሰራ መሆኑንና ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ውል በመግባት ተማሪዎች እንደተመረቁ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ  እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡