ከእንቦጭ አረም ይልቅ የምግብ ሰንሰለት ሥርዓት መዛባት የአባያ ሐይቅ ትልቁ ስጋት መሆኑ ተገለፀ፡፡ የሐይቁ ተፈጥሮም ከጣና ሐይቅ ጋር ሲነፃፀር ለእንቦጭ አረም ምቹ እንዳልሆነ ማወቅ ተችሏል፡፡በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የIUC ፕሮጀክት ኃላፊና የዘርፉ ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ በአባያ ሐይቅ ላይ በየቀኑ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ የሚነፍስ ከፍተኛ ማዕበል ወይም ነፋስ እንዳለ ገልፀው የማያቋርጠው ማዕበል አረሙን አንድ ቦታ ተረጋግቶ እንዳይቀመጥ በማድረግ ወደ ዳርቻ ያወጣዋል ብለዋል፡፡ ይህም አረሙ በሐይቁ ዳርቻ ላይ ብቻ እንዲታይና በሐይቁ ላይ እንዳይስፋፋ ማድረጉን ዶ/ር ፋሲል ይናገራሉ፡፡

እንደ ዶ/ር ፋሲል ገለፃ ከላይ በጠቀሱት ምክንያት እንቦጭ አባያ ሐይቅን ያጠፋዋል የሚል ስጋት ባይኖርም በሐይቁ ዳርቻ የሚገኘው እንቦጭ የሐይቁ ስጋት ስለሆነ አረሙን ለማጥፋት በዩኒቨርሲቲው ምርምር ዳይሬክቶሬት ፕሮፖዛል ተነድፎ የአረሙን ተፈጥሮና ባህሪ ጥናት ሙከራ ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ምናልባትም በሐይቁ ላይ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ የሚነፍሰው ማዕበል በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ቢቆም እንቦጭ ከጣና በባሰ መልኩ የአባያ ሐይቅ ስጋት ስለሚሆን አሁን ባለው ሁኔታ መዘናጋት አይገባም ብለዋል፡፡

በሐይቁ ችግሮች ዙሪያ ምርምሮችን እንደሠሩ የሚናገሩት ዶ/ር ፋሲል በጥናታቸው የሐይቁ የምግብ ሰንሰለት (Food Chain) መዛባቱን እንዳረጋገጡና ይህም ለሐይቁና በሐይቁ ውሰጥ ለሚገኘው ብዝሃ-ህይወት ትልቅ ስጋት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጥናታቸው መሰረት ለዚህ ችግር እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ከብላቴ ተፋሰስ ተጠርጎ የሚመጣው ቀይ አፈር ሲሆን በውስጡ አይረን ኦክሳይድ (iron oxide) የሚባለውን ንጠረ ነገር ወይም በተለምዶ ዝገት የያዘ በመሆኑ ንጥረ ነገሩ በሐይቁ ላይ በመንሳፈፍ የፀሐይ ብርሃን ወደ ሐይቁ እንዳይገባ ማድረጉ ነው፡፡

በጥናቱ እንደተረጋገጠው አሁን ባለው ሁኔታ በአባያ ሐይቅ ላይ የፀሐይ ብርሃን ከ10 ሴ.ሜ በላይ መግባት አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት በሐይቁ ውስጥ የፀሐይ ብርሃንን በመጠቀም ምግብ የሚያዘጋጁ እፅዋት እንዲሁም እፅዋቱን የሚመገቡ ሌሎች በውኃ ውስጥ የሚኖሩ እንስሳት እየጠፉና እየተመናመኑ ነው፡፡ የሐይቁ የዓሳ ሀብት የተመናመነው በዚህ ምክንያት ሲሆን ተንሳፋፊ ንጥረ ነገሮቹን ማፅዳት ከባድና አዳጋች በመሆኑ የምግብ ሰንሰለቱ ተዛብቷል፡፡

እንደ ተመራማሪው ማብራሪያ በሐይቁ ዙሪያና ተፋሰስ የነበሩት ደኖችና እፅዋት የሐይቁ ማጣሪያ ኩላሊቶች ሲሆኑ አሁን ያለው ሁኔታ ሁለቱ ኩላሊቶቹ ሥራ ካቆሙ ሰው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በሐይቁ ዙሪያና ተፋሰስ ከዛሬ 100 እና 200 መቶ ዓመት በፊት የነበሩትን ሀገር በቀል እፅዋት በመመለስ ሐይቁን ማዳን የሚቻል ሲሆን ካልሆነ ግን በሐይቁ ውስጥ ያለው ብዝሃ-ሕይወት የሚጠፋና ሐይቁም በጊዜ ሂደት ተመሳሳይ እጣ ፈንታ የሚደርስበት ይሆናል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የመፍትሔ ሀሳቦች እንዳሉ ሆነው ችግሮቹ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሚሠሩ ምርምሮችና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ብቻ የሚቀረፉ ባለመሆናቸውና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ በተለይ የፖለቲካ አመራሩን ቁርጠኝነት የሚጠይቁ ናቸው ሲሉ ዶ/ር ፋሲል አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡