የትምህርት ክፍሎችን የቀጣሪ ድርጅቶች የመቅጠር ፍላጎት መሰረት አድርጎ መክፈት የተለመደ አሰራር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ከትምህርት ሚኒስቴር በቀን 24/8/2005 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርመራ ለማድረግ ያስችለው ዘንድ 11 የትምህርት መስኮች እንዲከፈቱለት ጥያቄ ማቅረቡን የሚገልፅ ደብዳቤ ተልኳል፡፡ በዚህም መሠረት ዩኒቨርሲቲያችን ፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍልን መክፈት ያስችለው ዘንድ ሥርዓተ-ትምህርት በማዘጋጀት የውስጥና የውጪ  ግምገማዎችን በማስደረግና ሥርዓተ-ትምህርቱ ሌሎች ሂደቶችን እንዲያልፍ በማድረግ ፕሮግራሙን ከፍቶ ከ2007 ዓ/ም ጀምሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

ዩኒቨርሲቲው ፕሮግራሙ በዓይነቱ አዲስ በመሆኑ ለማስተዋወቅና በጋራ ለመስራት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ለአብነትም ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ከዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል እና ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን የተፈራረመበትን አውደ-ጥናት ሚያዚያ 21/2009 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

የትምህርት ፕሮግራሙን የመስተዋወቅ ሥራ በዩኒቨርሲቲው በስፋት ሲሰራ የቆየ ሲሆን በዚህ ረገድም ለፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ሚኒስቴር በማሳወቅ ፕሮግራሙ በአዲሱ የሥራ ደረጃ ምዘና አወሳሰን ዘዴ (JEG) ጭምር ደረጃና የሥራ መደብ እንዲወጣለት ተደርጓል፡፡

ነገር ግን ፋና ቴሌቪዥን በፋና 90 የዜና ፕሮግራም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፎረንሲክ ኬምስትሪና ቶክሲኮሎጂ ትምህርት ክፍልን አስመልክቶ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የትምህርት ክፍሉ ምሩቃን ብቸኛ ቀጣሪ መስሪያ ቤት አድርጎ በመውሰድ ካለው ስጋት አኳያ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጡ ተመራቂዎች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ከ2010 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት፣ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታና ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት የተሰጡ አስተያየቶችን ያካተተ ዘገባ አቅርቧል፡፡

በቀረበው ዘገባ የሥራ ዕድል ለማግኘት አልቻልንም ያሉት የዩኒቨርሲቲያችን የ2010 ዓ/ም ተመራቂዎችና ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው የዘርፉ ኃላፊዎች ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሊቀጥራቸው ፈቃደኛ አለመሆኑ፣ ከኮሚሽኑ ጋር የሚያሠራ የጋራ ውል ስምምነት አለመኖሩ፣ ለኮሚሽኑ ሥራ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል ከ100 የማይበልጥ ሆኖ ሳለ በተከታታይ በዚህ ዘርፍ ምሩቃን የሚሠሩበት ቦታ ሳይታወቅ ማስመረቅ ከፍተኛ ስጋት እንደሆነ ቀርቧል፡፡ ስለሆነም ከሥጋቱ አኳያ ምናልባት የትምህርት ክፍሉ የ1ኛ ዓመት ተማሪዎች ወደ Applied Chemistry ሊመደቡ የሚችሉበት ሁኔታ እንደ አስፈላጊነቱ ሊመቻች እንደሚችል እንዲሁም 2ኛና 3ኛ ዓመት ተማሪዎችንም አስመልክቶ ወደፊት አቅጣጫ እንደሚሰጥ ተጠቅሷል፡፡ ትምህርት ክፍሉም ተከፍቶ የተረሳም ነውም ተብሎዋል፡፡

ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲያችን ይህንን አዲስ ፕሮግራም በልዩ ትኩረት እየሠራ የሚገኝ ሲሆን የዘርፉ ተመራቂዎች የሥራ ማጣት ሥጋት እንዳይጋረጥባቸው በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሰሩ የሚያስችሉዋቸው ቅድመ ሁኔታዎች በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ሚኒስቴር በኩል እንዲጠናቀቁ ተደርጎ ለሚመለከታቸው ክፍሎች በደብዳቤ እንዲያውቁ ተደርጓል፡፡

በዚህም መሠረት የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር  ለዘጠኙ ክልሎችና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚዲካል ኮሌጅ፣ ለቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል፣ ለአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ለመላው አፍሪካ ስጋ ደዌ መከላከያና ት/መ/ማዕከል፣ ለኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ለመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኢንስቲትዩት፣ ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር የጤና ዋና ዳይሬክቶሬት፣ ለጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ለገፈርሳ የአዕምሮ ህሙማን ማገገሚያ ማዕከል፣ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የጤና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት፣ ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ለብሔራዊ ደም ባንክና ለኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ በፃፈው ደብዳቤ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በፎረንሲክ ኬሚሰትሪና ቶክሲኮሎጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎችን ያስመረቀ መሆኑን በመጥቀስ ሙያው በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ሚኒስቴር ተገምግሞ የጤና ሙያ ሆኖ የተመዘገበ መሆኑን በመግለጽ በሙያው የተመረቁ ባለሙያዎች እንደማንኛውም የጤና ሙያ ሆኖ ባሉ ክፍት መደቦች ተቀጥረው እንዲሰሩ እንዲደረግ አሳውቋል፡፡

ምንም እንኳ እንደ አገር የሚታየው የሥራ ዕድል አለመቻቸትና ተመራቂዎች ወደ ሥራው ዓለም ወዲያው ያለመቀላቀል ችግር በሂደት የሚፈታ ቢሆንም ከተመራቂዎቻችን መካካል 7ቱ በዩኒቨርሲቲያችን በረዳት መመህርነት የተቀጠሩ ሲሆን 5ቱን ደግሞ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የፎረንሲክ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት በዩኒቨርሲቲያችን ተመልምለው በረዳት መመህርነት እንዲቀጠሩ ተደርጎ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ሌሎቹ ተመራቂዎችም በሂደት ወደ ሥራ ዓለም እንደሚቃላቀሉ የፀና እምነት አለን፡፡

በሌላ በኩል ማንኛውም መ/ቤት በዘርፉ ባለሙያ በሚቀጥርበት ጊዜ ከመስኩ ሥራ ሥነ-ምግባር፣ ክሂሎት፣ ግንዛቤና መሰል ጉዳዮችን የተመለከቱ ደመወዝ የሚከፈልባቸው ሥልጠናዎችን የሚያመቻች መሆኑ እየታወቀ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን  ለተመራቂዎቻችን ሊሰጥ የፈለገውን ሥልጠና አለመውሰድ ተገቢ አለመሆኑን እናሳውቃለን፡፡

በመጨረሻም በፋና 90 በቀረበው ዘገባ የትምህርት ክፍሉን አስመለክቶ የተፈጠረው የግንዛቤ ክፍተት በዚሁ እንዲታረም እንዲሁም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንም ተጨማሪ ዘገባ በማዘጋጀት የተፈጠረውን ብዥታ እንዲየጠራ እንጠይቃለን፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት