በዩኒቨርሲቲው የድህረ-ምረቃ ት/ቤት አስተባባሪነት ‹‹የዶክተሮች ቀን›› የተመለከተ የምርምር አፈፃፀም ግምገማና ውይይት ኅዳር 28/2011 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡

ፕሮግራሙ በተለያዩ ዘርፎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ የሦስተኛ ዲግሪ የጥናትና ምርምር ሂደት አፈፃፀም፣ የሱፐርቫይዘሮች እና የምሩቃን ጉዳይ ኮሚቴ ሚና በተመለከተ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመገምገም ለቀጣይ ሥራዎች ግብዓት የሚሆን መረጃ በመለዋወጥ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖር ለማስቻል መሆኑን የድህረ ምረቃ ት/ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር አበራ ኡንቻተናግረዋል፡፡ የድህረ ምረቃ ት/ቤት ቀደም ሲል የነበረውን አደረጃጀት ለማሻሻልና የአሠራር ሥርዓቱን በአዲስ መልክ በማዋቀር ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን ለሚደረገው ሂደት ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሀሳቦችንም ለማግኘት እንሚረዳ ዶ/ር አበራ አክለዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው በአካዳሚክ ዘርፍ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመክፈት ተማሪዎችን በማስተናገድ ረገድ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብና በስትራቴጂክ እቅድ ዘመኑ መጨረሻ 163 ተማሪዎችን በሦስተኛ ዲግሪ ለማስተናገድ የታሰበ ሲሆን አሁን ባለው አፈፃፀም የሚያበረታታ እምርታ እንደተመዘገበ ገልፀዋል፡፡

ፕሮግራሞችን በመክፈት ረገድ  ያለው አፈፃፀም መልካም ቢሆንም በተለያዩ የትምህርት መስኮች የተከፈቱ የትምህርት ፕሮግራሞች በአተገባበር ይዘታቸው አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ደረጃ እንዲኖራቸው የማድረጉ ሥራ ትልቅ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ ይህ የዶክተሮች ቀን ፕሮግራም የተጀመረው ሂደት ከግብ እንዲደርስ ድርሻው የጎላ እንደሆነና እንደ ዩኒቨርሲቲ ብሎም በኢንስቲትዩት፣ በኮሌጅና በትምህርት ቤት ደረጃ የምርምር ሥነ-ምህዳሩ ላይ እየታየ ላለው እምርታ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን አጠቃላይ  ይዘትና አፈፃፀም በተመለከተ በትምህርት ቤቱ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ በዚህም በት/ቤቱ የሚሰጡ የ2ኛና የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን በተመለከተ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ውስንነቶች በዶ/ር አበራ ኡንቻ ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም በኢንስቲትዩት፣ በኮሌጆችና በት/ቤቶች ባሉ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ከሚሠሩ ጥናትና ምርምሮች መካከል ለፕሮግራሙ የተመረጡ አፈፃፀሞች ሪፖርት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡

በዶክትሬት ተማሪዎች በቀረበው የምርምር አፈፃፀም፣ በመማር ማስተማር፣ በመልካም አስተዳደር፣ በገምጋሚ አካላት አወቃቀር እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በተማሪዎችና በተሳታፊ አካላት ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡

በቀረቡት አስተያየቶችና ጥያቄዎች መነሻነት ፕሬዝደንቱን ጨምሮ በሚለከታቸው አመራሮች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን በፕሮግራሞቹ በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ራሳቸውን በላቀ የአካዳሚክና የጥናትና ምርምር ከፍተኛ ሙያ ባለቤት ለመሆን እየሠሩ እንዳሉ መገንዘብ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በመማር ማስተማሩ ሂደት ውጣ ውረዶች እንዳሉ ቢታወቅም ይህ ሳይገድባቸው ለውጤትና ለተሻለ አፈፃፀም መትጋታቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር እንደሆነ እና በቀጣይ ዩኒቨርሲቲው በጋራ በመመካከር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሠራም ተገልጿል፡፡

ተሳታፊዎችም ይህን በዓይነቱ በዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ የሆነው ‹‹የዶክተሮች ቀን›› መካሄድ መቻሉ ትልቅ አንድምታ ያለውና በኢንስቲትዩት፣ በኮሌጆችና በት/ቤቶች ያሉ ተማሪዎች የጥናትና ምርምር ውጤቶች ላይ በመወያየት ሀሳብ ለመለዋወጥ ብቻም ሳይሆን እርስ በእርሳቸው እንዲቀራረቡ በማድረግ በሁሉም ዘርፍ ለሚመዘገቡ ውጤቶች ስኬት አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ በዩኒቨርሲቲው በማስተማር ላይ ያሉ ዶክተሮችና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡