የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት በዩኒቨርሲቲው ያለውን አሠራር በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ገለፀ፡፡

ዳይሬክቶሬቱ የመማር ማስተማር ሂደቱን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ ዓላማው እንደሆነ የገለፁት የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ታደሰ በግቢ ውስጥ ያለውን የዋይፋይ አገልግሎት ከማስፋት አኳያ ተጨማሪ መሣሪያዎች ባለመገዛታቸው ለተማሪዎች በየካምፓሱ ተጨማሪ የማስፋፊያ ሥራ መሥራት አልተቻለም ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ፋይበር ገመዶች ሆን ተብሎ እና በዕውቀት ማነስ ምክንያት እንዲሁም በኮንስትራክሽን ድርጅቶች በተደጋጋሚ የሚቆረጡ በመሆኑ የኔትወርክ መቆራረጥ ይገጥማል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ባሉ ውስን ባለሙያዎች ጥገና እየተካሄደ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዳይቋረጥና 400 MB የነበረውን የኢንተርኔት ፍጥነት በእጥፍ በማሳደግ በቅርቡ 800 MB ለማድረስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የዲጂታል ቤተ-መጽሐፍት አገልግሎትን ተማሪዎች በሁሉም ካምፓሶች ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡ ሰዎችን ለመቆጣጠር እና ተማሪዎች ካፊቴሪያ፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ ክሊኒክ በመሳሰሉት ቦታዎች የሚገለገሉባቸው የበር ላይ ፍተሻ ማሽኖች (One Id Card System) ያለምንም ሥራ መቆማቸውን በተመለከተ የሰው ሀብት አስ/ል ዳይሬክቶሬት እና የፀጥታና ደኅንነት ጽ/ቤት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ከተወጡ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

የሠራተኞችን ክሂሎት ከማሳደግ አኳያ ዳይሬክቶሬቱ ለአስተዳደር ሠራተኞችና ለመምህራን E-learning፣ ቪዲዮ መሥራትና አፕሎዲንግ፣ ቪዲዮ ኮንፈራንስ ማዘጋጀት እና በመሳሰሉት ላይ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

ከጥገና ጋር በተያያዘ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተሻለ ያሉንን ሀብቶች አሟጠን እንጠቀማለን ያሉት ዳይሬክተሩ ለዚህም ማሳያ ከ15 ዓመት በላይ የቆዩ ፕሪንተሮችና የኮፒ ማሽኖችን እየጠገንን መጠቀማችን ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ካስፐርስኪ አንቲቫይረስን መጠቀም ከጀመረ በኋላ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉ ኮምፒውተሮች ብልሽትና ዳግም ወጪ መቀነሱንም ተናግረዋል፡፡