ከ875 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት በ2007 ዓ/ም በ6 ሄክታር መሬት የግንባታ ሥራው የተጀመረውና በ2 ዓመት ከ5 ወር ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው ዘመናዊ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል በአገራዊ የገንዘብ ግሽበትና የእቃዎች ዋጋ መናር ምክንያት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ አለመቻሉን የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ገለጸ፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የቢዝነስና ልማት ም/ፕዝደንት ተወካይ ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን እንደገለጹት ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማስጨረስ ዩኒቨርሲቲው በ2011 በጀት ዓመት ከጠየቀው 450 ሚሊየን ብር በጀት በፌዴራል መንግሥት የተፈቀደው 166 ሚሊየን ብር ብቻ ሲሆን ይህም ገንዘብ ቢሆን በወቅቱ ሊለቀቅ አልቻለም፡፡ የበጀት ችግሩ እንዳለ ሆኖ ከተቋራጭ ድርጅቱ ጋር መግባባት በመፍጠር በተቻለ መጠን ሥራዎች አየተሠሩ መሆኑን ተወካይዋ ተናግረዋል፡፡

ከአገር አቀፍ የገንዘብ እጥረቱ በተጨማሪ የዲዛይን ሥራዎች እና በሆስፒታሉ ዙሪያ የድንበር ማካለሉ ሥራ ሙሉ ለሙሉ አለመጠናቀቅ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቅ ካደረጉ ምክንያቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ድንበር ማካለሉን አስመልክቶ በሆስፒታሉ ዙሪያ ከይዞታቸው ተነሺ ከሆኑ 60 መኖሪያ ቤቶች ለ47ቱ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ጋር በመሆን ተመጣጣኝ ተለዋጭ የመኖሪያ ቦታ ተመርጦ የዲዛይኑ ሥራ ያለቀ ሲሆን በዩኒቨርሲቲውና በከተማው ማዘጋጃ ቤት ትብብር ለነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለማከናወን በሂደት ላይ ነው፡፡ ለቀሪዎቹ ተነሺ ነዋሪዎችም ለመኖሪያ ቤት የሚሆን የቦታ መረጣ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የሆስፒታሉን ግንባታ በማከናወን ላይ የሚገኘው ይርጋለም ኃ/የተ/የግል ማኅበር መሀንዲስ ይህደጎ ተስፋዬ እንደተናገሩት የግንባታ ሥራዎች በታቀደላቸው ጥራት በመከናወን ላይ ቢገኙም በዩኒቨርሲቲው በኩል የሚለቀቀው ገንዘብ ወቅቱን ጠብቆ አለመድረስ፣ በአማካሪው በኩል የዲዛይን ሥራዎች ሙሉ በሙሉ አለማለቅ እንዲሁም የድንበር ወሰን ማካለል ችግር ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዳይጠናቀቅ ምክንያቶች ሆነዋል፡፡ የጋዝና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሲስተሞቹ በሪፈራል ሆስፒታል ግንባታዎች ከተሰማራንባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ ዘመናዊነትን የተላበሱ ናቸው ያሉት መሀንዲሱ በአጠቃላይ ሊገነቡ ከታሰቡት 11 ግንባታዎች የሪፈራል ሆስፒታሉ ዋና ህንፃ፣ የአካል ጉዳተኞች መወጣጫ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ብቻ ግንባታቸው ከ90% በላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ በማድረግ 7 የመወጣጫ ሊፍትና ከ00 አልጋዎች ያሉት ዘመናዊው ሆስፒታል በውስጡ መረጃዎች በዘመናዊ መልክ የሚደራጁበት Data System፣ ህመምተኞች በቀላሉ የህክምና ባለሙያዎችን የሚጠሩበት Nurse Call System፣ የሆስፒታሉን ደኅንነት የሚቆጣጠሩ Digital Camera System፣ ታካሚዎችን የሚያዝናኑና በቂ መረጃን የሚሰጡ Tv System እና መሠል ዘመናዊ ሲስተሞች የተገጠሙለት ነው፡፡

የዘመናዊውን የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች  ኮርፖሬሽን የማማከር ሥራ የሚሠራለት ሲሆን ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለመማር ማስተማር ሂደት አጋዥ ከመሆኑም በተጨማሪ ለምርምር ሥራ መዳረሻ እንደሚሆን  ይሆናል፡፡