የፌዴራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና የኃይማኖት አባቶች ጋር በ2011 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ  ውይይት አካሂደዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

ውይይቶቹ 2011 የትምህርት ዘመንን ውጤታማና ሠላማዊ ለማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት በተደራጀ ሁኔታና በቅንጅት ለመስራት የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር በማለም የተፈፀሙ መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት / ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡

ለሚነሱ ጥያቄዎች ወቅቱን የጠበቀ ምላሽ አለመሰጠት፣ በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ያለው የደኅንነት ስጋት፣ wi-fi አገልግሎት የተማሪዎች ማደሪያ አካባቢ ባለመኖሩ ለሴትና አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በምሽት ለመጠቀም አስቸጋሪ መሆን፣ ለተግባር ትምህርት የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን በመድረኩ ከተማሪዎች ከተነሱ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘደንት / ዳምጠው ዳርዛ በሰጡት ምላሽ ችግሮቹን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ተግባራትን 100 ቀን ዕቅድ በማካተት እየሠራ ሲሆን እንደተለመደው ዩኒቨርሲቲውን ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሥፍራ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ንግድና ኢንደስትሪ ሚነስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች በኩል የተነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ በቅንጅትና በትኩረት እንዲሠራ አሳስበው ተማሪዎች በአንፃሩ ደግሞ ራሳቸውን ከአልባሌ ነገሮች በማራቅ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ለውጡን የማይፈልጉ በርካታ ኃይሎች መኖራቸውን ያስታወሱት ሚነስትር ዴኤታው በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠሩት ችግሮች እነዚህ ኃይሎች ዩኒቨርሲቲዎችን መጠቀሚያ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ለመሆናቸው ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡ ተማሪወች የለውጥ ቀልባሽ ኃይሎችን ሀሳብ ባለመሸከም ዩኒቨርሲቲውን የሠላም ማዕከል ለማድረግ ከብሄርተኝነት በመራቅና የመቻቻል ባህልን በማጎልበት ከለውጡ ጎን መሆናቸውን በተግባር ሊያሳዩ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡