ለዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ተማሪዎች በውጭ አገር የትምህርት ዕድል አሰጣጥ፣ የቪዛ ሂደት፣ በመምህራን ልምድ ልውውጥ፣ በውጭ አገር ተቋማት የሥራ እድል በማመቻቸት እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የልምድ ልውውጥ የውይይት መድረክ ከታኅሣሥ 12-13/2011 ዓ/ም በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የትምህርት ዘርፍ አማካሪ ይካሄዳል ፡፡

ፕሮግራሙ በአሜሪካ ኤምባሲ የህዝብ አስተዳደር ጉዳይ ክፍል ሥር በአዲስ አበባ የሚገኘው የትምህርት ማማከር አገልግሎት ማዕከል በኩል ተማሪዎች በተለያዩ የዓለም አገራት ዕውቅና ባላቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተዓማኒ፣ ሁሉን አቀፍ እና ወቅታዊ መረጃ ባለው መልኩ የትምህርት ዕድሎቻቸውን እንዲያገኙ የሚያግዝ ነው፡፡

በመድረኩ ለተማሪዎች የተለያዩ የስኮላርሽፕ አማራጮችን ማመቻቸት፣ የስኮላርሽፕ ማመልከቻና የቪዛ ሂደት፣ የ globalUgrad ፕሮግራም የተሳትፎ መስፈርቶች፣ የፈተና አሰጣጥ፣ የገንዘብ ድጋፍ እና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች ተካተውበታል፡፡ በተጨማሪም ከትምህርት ዕድል አሰጣጥ ጋር በማዕከሉ በቡድን እና በግለሰብ ደረጃ የማማከር አገልግሎቶችን በተመለከተም ገለፃ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ የውጪ አገር ተቋማት የሥራ ፍለጋ፣ የመምህራንና ተማሪዎች ልምድ ልውውጥ (staff exchange) እና በአሜሪካ ለአንድ መንፈቀ ዓመት ሙሉ ወጪው የሚሸፈን የትምህርት ዕድል የሚያስገኙ መልካም አጋጣሚዎችንም ያካተተ ነው፡፡

በመሆኑም በፕሮግራሙ በሁሉም ዘርፍ ላይ ያላችሁ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እንዲሁም የመጀመሪያ ዲግሪ እና የድህረ ምረቃ ተማሪዎች እንድትሳተፉ ተጋብዛችኋል፡፡

በዚህም መሠረት ፕሮግራሙ፡- በዩኒቨርሲቲው በየዘርፉ ላሉ መምህራን ዓርብ ከሰዓት 8፡30 ጀምሮ በዋናው ግቢ መሰብሰቢያ አዳራሽ እንዲሁም ለሁሉም የመጀመሪያ እና የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ቅዳሜ ጧት ከ2፡30-04፡00 ድረስ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ይህ መልካም ዕድል እንዳያመልጥዎ ይሳተፉ!!
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ