ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም ለቡድን መሪዎችና የዕቅድ ባለሙያዎች የፕሮግራም በጀት ይዘት፣ አሠራርና አስተዳደር የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና ታኅሣሥ 05/2011 ዓ.ም ተሰጥቷል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

ሥልጠናው በፕሮግራም በጀት አዘገጃጀትና አስተዳደር ረገድ ያለውን ክፍተት ለመሙላት፣ ግንዛቤ ለማዳበር፣ ዕቅድን ከበጀት ጋር አጣጥሞ ከመተግበር አኳያ ያለውን ክፍተት ለማስተካከል፣ አሳታፊ የበጀት አዘገጃጀትና አስተዳደር በመተግበር የፋይናንስ ግልጽነት ተጠያቂነትን ለማጠናከር፣ ለሥርዓተ-ፆታ ምላሽ ሰጪ በጀት ዝግጅትና አስተዳደር ለማረጋገጥ እንዲሁም የፋይናንስ፣ የንብረት አስተዳደርና የግዥ አዋጆች፣ መመሪያዎችና ደንቦች አተገባበርን በማጠናከር በበጀት ላይ የሚያዙ ኃላፊዎችን ከስህተት ለመጠበቅ ያለመ ነው ሲሉ የስ/ዕ/ዝ/ክ/ግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ ገልፀዋል፡፡

በሥልጠና ሰነዱ እንደተብራራው በጀት መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የልማት ሥራዎች ትኩረት በመስጠት የሚዘጋጅ የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ሲሆን ውጤታማ የሆነ የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሥርዓት መኖሩ መንግሥት ለዜጎች የገባውን ቃል እንዲጠብቅና ግዴታውንም እንዲወጣ ያስችለዋል፡፡ የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለበት ዜጎች ጥቅም ላይ የዋለውን ሀብትና በመንግሥት በጀት ቃል የተገባውን የአገልግሎት አቅርቦት ደረጃ መከታተልና መብታቸውን መጠየቅ አይችሉም፡፡

የበጀት ግልጽነት ዳሰሳ ጥናት ሙስና እና ብክነት የበዛበት ወጪ ይቀንሳል፤ በዜጎች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የሚፈለጉ ወጪዎች ከአገሪቱ ሀብት ጋር ማጣጣም ያስችላል፤ ለዓለም አቀፍ የፋይናንስ ገበያ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የብድር  አስተዳደርን ያሻሽላል እንዲሁም በዜጎች እና በመንግሥት መካከል መተማመንን ከመፍጠሩም በላይ ለፖሊሲ ውሳኔዎች ቅድሚያ ለመስጠት ያስችላል፡፡

ማኅበራዊ ተጠያቂነት ዜጎች ቀልጣፋ፣ የተሟላና የተሻሻለ መሠረታዊ አገልግሎት በመንግሥት እንዲቀርብላቸው እና አገልግሎት አቅራቢው አካልም ለሚያሳየው ደካማ አገልግሎት አሰጣጥም ሆነ ጉድለት ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል  የአሠራር ሂደት ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የሥልጠናውን ይዘት ሁሉም አካላት አስፈላጊነቱን በመገንዘብ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ወደ ተግባር ለመቀየር መሥራት የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሠልጣኛች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ከመድረኩ ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡