ግርጫ የደጋ ፍራፍሬና አትክልት ምርምር ማዕከል የተሻለ ምርት የሚያስገኙ ምርጥ የፍራፍሬና የአትክልት ዝርያዎችን በምርምር ማግኘቱን አስታወቀ ::ግርጫ የደጋ ፍራፍሬና አትክልት ምርምር ማዕከል ለአካባቢው የአፈርና አየር ፀባይ ተስማሚ፣ ምርታማና በሽታን መቋቋም የሚችሉ አምስት የፍርፍሬና የአትክልት ዝርያዎችን በምርምር ማግኘቱንና ዝርያዎቹን ለህብረተሰቡ ለማሰራጨት በዝግጅት ላይ መሆኑን አሳውቋል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ከበደ ጆቢር እንደተናገሩት በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን ችግር ለመፍታት በርካታ የምርምር ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በማዕከሉ ከሚደረጉ የምርምር ሥራዎች መካከል ለአካባቢው አፈርና  የአየር ፀባይ ተስማሚና ምርታማ የሆኑ ዝርያዎችን በምርምር መለየትና የተሻሉትን  ለህብረተሰቡ አባዝቶ በማዳረስ ተጠቃሚ ማድረግ  ዋነኛው የማዕከሉ ትኩረት ነው፡፡

ዶ/ር ከበደ በማዕከሉ ተመራማሪዎች በተደረገው ጥናት “crispin” እና “Royal gala” የተባሉ የአፕል ዝርያዎች፣ ‹‹ጉደኔ›› የተባለ በሄክታር እስከ አንድ መቶ ኩንታል ማስገኘት የሚችል የድንች ዝርያ፣ ‹‹ሊንዳ›› የተባለ አንዱ ከ10 ኪ.ግ በለይ የሚመዝን የጥቅል ጎመን ዝርያ፣ A-108 የተባለ የካሮት ዝርያ እንዲሁም ሌሎች የሰላጣ እና የቀይ ሥር ዝርያዎች  ለአከባባቢው የአየር ፀባይና አፈር ተስማሚና ምርታማ እንዲሁም በሽታ የሚቋቋሙ መሆናቸው በምርምር በመረጋገጡ ዝርያዎቹን አባዝቶ ለአካባቢው ማህረሰብ ለማከፋፈል ይረዳ ዘንድ ዝርያዎቹን የማባዛት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በአካባቢው እስካሁን ባለው አፕል የማምረት ሂደት ውስጥ የትኛው መሰረተ-ግንድ ከየትኛው ፍሬ ከሚሰጠው ዝርያ ጋር ተዳቅሎ የተሻለ ምርት ወይም ፍሬ ይሠጣል የሚለው ባለመታወቁ ምርምሩን ለመስራት መነሳሳት መፍጠሩን የተናገሩት ዶ/ር ከበደ በሂደቱም በርካታ ዝርያዎችን በማሰባሰብ ለመሰረተ-ግንድ የሚያገለግሉ ዝርያዎችን በማሳደግና  ለፍሬ ከሚያገለግሉ ሌሎች ዝርያች ጋር በማዳቀል ዕድገታቸው ላይ በተከታታይ ክትትል ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በተደረገው ክትትልም ከዝርያዎቹ መካከል በቅጠልና በአበባ መጠኑ እንዲሁም በፍሬ መጠናቸው “crispin” እና “Royal gala” የተባሉ ዝርያዎች የተሻሉ ሆነው መገኘታቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በድንች ላይም ተመሳሳይ የምርምር ሂደት ተግባራዊ እንደተደረገ ያስረዱት ዶ/ር ከበደ በሂደቱም በሀገሪቱ ከሚገኙ የምርምር ማዕከላት ከተሰበሰቡ  6  ምርጥ የድንች ዝርያዎች መካከል ለአካባቢው አፈርና የአየር ፀባይ ተስማሚና  ምርታማ የሆነውን ለመለየት ምርምሩ ተከናውኗል፡፡ በተደረገው ክትትልም ‹‹ጉደኔ›› የተባለው የድንች ዝርያ በርካታ ምርት ማስገኘት ከመቻሉም ባሻገር ለአካባቢው የአየር ንብረትና አፈር ተስማሚና በሽታ የሚቋቋም መሆኑ በጥናቱ በመረጋገጡ ይህንን ዝርያ አባዝቶ 120 ለሚጠጉ ወጣት አርሶ አደሮች ሥልጠና በመስጠት ዘሩን ለማከፋፈል እየተሰራ መሆኑን ዶ/ር ከበደ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ጉደኔ›› በተባለው የድንች ዝርያ ነባሩን የአካባቢው አርሶ አደር የሚጠቀምበትን የድንች ዝርያ ሙሉ በሙሉ ለመተካትም ይሰራል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት