የBenefit-Realise (ቤኔፊት-ሪያላይዝ) ፕሮጀክት ክልላዊ የዕቅድ አውደ ጥናት ተካሄደ

የአርባ ምንጭና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ በመተባበር የBenefit-Realise (ቤኔፊት- ሪያላይዝ) ፕሮጀክት ክልላዊ የዕቅድ አውደ ጥናት የካቲት 6/2011 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ከተማ በኃይሌ ሪዞርት አካሂደዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ቤኔፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር መብራቱ አለሙ የአውደ ጥናቱ መሠረታዊ ዓላማ በዕቅዱ ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየትና ግብዓቶችን በማሰባሰብ አሳታፊ ዕቅድ አዘጋጅቶ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እና የፕሮዳክሽን ሴፍትኔት ፕሮግራም /PSNP/ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግ ወጪያቸውን ማስተካከል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ምስሉን ለማየት ከዚህ ይጫኑ

አገር አቀፍ  የሪያላይዝ  ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ቴዎድሮስ ተፈራ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በ60 ወረዳዎች፣ በ4 ክልሎች እና በ8 ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮግራሙን ተግባራዊ እያደረገ ሲሆን ትኩረቱም አነስተኛ መሬትና ውሃን ተጠቅሞ  አጥጋቢ  ምርት ማምረት እንደሚቻል ለአርሶ አደሩ ማሳየት እንዲሁም  የግብርና ምርትን ውጤታማ ማድረግና በምግብ እጥረት የተጎዱ ወረዳዎችን በሴፍትኔት ፕሮግራም አማካኝነት መርዳት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የተሻሉና ውጤታማ ተሞክሮዎችን ማካፈልና ፈጠራን ማበረታታት እንዲሁም የባለሙያዎችንና የተቋማትን አቅም ማጎልበት ወሳኝ እንደሆነ የገለፁት ዳይሬክተሩ ፕሮጀክቱ በክልል ደረጃ ከግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ፣ ከክልል እርሻ ምርምር ተቋማት RARIS እና PSNP የሴፍቲኔት ዳይሬክቶሬቶች የፕሮግራሙ አጋር በመሆናቸው በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የፕሮዳክሽን ሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ክላስተር 4  በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ክላስተር 6 ወረዳዎችን መሰረት ያደረጉ የተሻሉ ተሞክሮዎችን በመለየት ለአርሶ አደሩ በማድረስ፣ በቂና  ጥራት ያለውን ዘር በማቅረብ፣ የምግብ ዋስትና ችግሮችን በመቅረፍ እንዲሁም የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበትና የአየር ፀባይ ተፅዕኖን በመቀነስ ላይ ያተኮሩ ተግባራትን ያካተተ የሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች የፕሮጀክቱ ዓመታዊ ዕቅድ በፕሮግራሙ አስተባባሪዎች አማካኝነት ቀርቦ የተገመገመና አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን በዕቅዱ  ሳይካተቱ የቀሩ ጉዳዮች እንዲካተቱ ጥቆማ ተደርጓል፡፡
በዋግኒንገን ዩኒቨርሲቲ የልማትና አዳዲስ ግኝቶች ማዕከል የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ አማካሪ Nina de Roo በመዝጊያ ንግግራቸው በግብርናው መስክ ጠንክረው የሚሰሩ አርሶ አደሮች ቢኖሩም የእውቀት ክፍተት እንደሚስተዋልባቸው ጠቁመው የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማስተዋወቅ ሙያዊ ዕገዛ ከተደረገላቸው ምርታማ ስለሚሆኑ ህይወታቸው በቀላሉ ይቀየራል ብለዋል፡፡
በዕለቱ ከዓለም አቀፍ ፕሮግራም ማኔጅመንት ዩኒት፣ ከዋግኒንገን ዩኒቨርሲቲና፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ  ድርጅቶች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡