የተቋማዊ ጥራት ማበልፀጊያ ዳይሬክቶሬት ከዩኒቨርሲቲው ለተወጣጡ 165 መ/ራን የጥራት ማረጋገጥና የፕሮግራም ኦዲት ስልጠና ከየካቲት 21-22/2011 ዓ/ም ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሰጥቷል፡፡
የተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም እንደተናገሩት የስልጠናው መሰረታዊ ዓላማ በፕግራም ግምገማ ላይ ለመ/ራን በቂ ዕውቀትና ክህሎት በማስጨበጥ ፕሮግራም ኦዲት ማድረግ እንዲችሉ ማብቃት ነው፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ ስልጠናውን ተጠቅመው የተለያዩና የተመረጡ ፕሮግራሞች ያሉበትን ደረጃ እና የጥራታቸውን ሁኔታ መፈተሽና ማሻሻያዎችን ማድረግ ነው፡፡ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት በአገራችን ላለፉት 20 ዓመታት በትምህርት ተደራሽነት ላይ በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን በሂደቱ የተገኘው ውጤትም ለአገሪቱ ልማትና እድገት እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው፡፡ ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች ምላሽ የሚሹ በመሆናቸው ከትምህርት ፕሮግራሞች፣ ከተመራቂ ተማሪዎች ብቃት፣ ከቤተ-ሙከራ፣ ከተግባር ትምህርት እንዲሁም ከሰው ኃይል አኳያ በአግባቡ መዘጋጀትና መፈተሽ ይኖርብናል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው መሰረታዊና ወቅታዊ በመሆኑ ለመ/ራን መሰጠቱ በትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ለሚደረጉ የማሻሻያ ሥራዎች ጉልህ ሚና የሚጫወትና የመማር ማስተማር ክሂሎትን አሳድጎ ሙሉ ባለሙያ የሚያደርግ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ /HERQA/ የጥራት ኦዲትና አቅም ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ዶ/ር ድንኳና ንጉሳ በከፍተኛ ተቋማት ጥራትን ይህ ነው ብሎ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ እንደሆነ ገልፀው ኤጀንሲው እየተጠቀመ ያለው የጥራት ፍቺ ለዓላማው / Fit for purpose/ ብቁ ሆነው እንዲገኙ ማስቻል ነው ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ጥራት በሚሠራው በእያንዳንዱ ሥራ ላይ በሂደት የሚረጋገጥ ሲሆን ከግብዓት ጀምሮ የመማር ማስተማር፣ የማኅበረሰብ አገልግሎትና የምርምር ዘርፉ ለዚያ ብቁ መሆኑን ማረጋገጥና በምን ደረጃ ጥራቱ እንደሚረጋገጥ ማሰብ ያሻል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተገቢውን እውቀት፣ ክሂሎትና አመለካከት የያዙና ኢኮኖሚውን የሚመጥኑ ተመራቂዎችን አሰልጥነው ካወጡ ጥራት ያለው ባለሙያ አሰልጥነዋል ማለት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ዶ/ር ድንኳና አክለውም በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ የሚወጣ ተመራቂ የሚፈለግበትንና መጀመሪያ የተቀመጠውን ግብ መምታት ከቻለ ተቋሙ ጥራት ያለው ተመራቂ አብቅቷል ብለዋል፡፡

በኤጀንሲው የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አቅም ማጎልበት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አሰልጣኝ አበባየሁ ተፈራ እንዳብራሩት እንደ ኤጀንሲው ጥራት ማለት እያንዳንዱ ፕሮግራም ሲከፈት ሥርዓተ ትምህርቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት ሥራዎች መሠራታቸውንና ውጤታማ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ በተጨማሪም የተቋማዊ ጥራት ኦዲት በተቋም ደረጃ የሚታይ ሲሆን የፕሮግራም ጥራት ኦዲት ማለት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ያሉ ፕሮግራሞች ኦዲት የሚደረጉበት ነው፡፡ የጥራት ጉዳይ አንዴ ተሠርቶ የሚቆም ባለመሆኑ በተደጋጋሚ ኦዲት የሚደረግ መሆኑን የጠቆሙት አሰልጣኙ እንደ አሠራር ፕሮግራሞች በተደጋጋሚ ኦዲት ሲደረጉ የመገምገሚያ መስፈርታቸው የተለያየ እንዲሆን ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በተቋም ደረጃ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ኦዲት የተደረጉ ሲሆን በፕሮግራም ደረጃ ግን ምህንድስናና ጤና ሳይንስ ዘርፎች ብቻ ኦዲት መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡

ሌላኛዋ የኤጀንሲው አሰልጣኝ ወ/ሪት ትዕግስት ኃ/ሥላሴ የኤጀንሲውን ዋና ተልዕኮ ሲገልፁ የመንግሥትም ሆነ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡት ትምህርት አግባብነትና ጥራት ያለው መሆኑን ከማረጋገጥ ባሻገር ፈቃድ ይሰጣል፤ ያድሳል፤ አነስተኛ የደረጃ መለኪያውን የማያሟሉትን ይከለክላል፤ የውስጥ ጥራት ማስጠበቂያ ሥርዓት እንዲዘረጋ ድጋፍ  ያደርጋል፤ ማንዋሎችን በማዘጋጀትና ስልጠና በመስጠት እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ጥራት ትልቅ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባና  የትምህርት ጥራት እንዲመጣ ከትምህርት ክፍል ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ወጥ የሆነ ግንዛቤ ሊኖር እንደሚገባ አሰልጣኟ ተናግረው ከአደረጃጀት አንፃር በዋናነት ኃላፊነቱን ወስዶና ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ የሚሠራ አካል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በመዝጊያ ንግግራቸው ተወዳዳሪ፣ ተፎካካሪና ተመራጭ ካልሆንን እንደዩኒቨርሲቲ ለመቀጠል አስቸጋሪ በመሆኑ መዋቅሩን በማስፋፋት ሁላችንም ለጥራት ትኩረት ሰጥተን መሥራት አለብን ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ስልጠናውን የወሰዱ መ/ራን ስልጠናውን ላልወሰዱት መ/ራን መረጃውን ተደራሽ በማድረግ የተገኘውን ግንዛቤ ወደ ተግባር ቀይሮ መሥራት ላይ ግንባር ቀደም እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

ሰልጣኝ መ/ራን በሰጡት አስተያየት ስልጠናው የተለያዩ ፕሮግራሞችን እንዴት መገምገም እንደሚቻል በቂ ግንዛቤን የፈጠረ ከመሆኑም በላይ በቀጣይ የመማር ማስተማር ስራ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆንና የበለጠ እንዲተጉ የሚያነቃ ነው ብለዋል፡፡

የጥራት ቁጥጥርና አሠራር፣ የተከታታይ ምዘና አዘገጃጀት፣ የምዘና ጥራት ቁጥጥር የመሳሰሉ ርዕሶች በስልጠናው በስፋት ተቃኝተዋል፡፡ በስልጠናው ሂደት የተለያዩ የግልና የቡድን ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡  በስልጠናው መጨረሻም ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡