አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጫሞና አባያ ሐይቆች ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም መንስኤ፣ መጠን፣ ስርጭት፣ ተፅዕኖና የመከላከያ ስትራቴጂዎች ለማወቅ የሚያግዝ የምርምር ፕሮጀክት መጋቢት 4/2011 ዓ/ም በይፋ ጀምሯል፡፡ የምርምር ሥራው የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን በጥናቱ ስድስት የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ምስሎቹን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የምርምር ቡድኑ አባል ዶ/ር ተሾመ ይርጉ የአባያና ጫሞ ሐይቆች በተለያዩ ምክንያቶች ሥነ-ምህዳራቸው መጎዳቱና በተለይ በአባያ ሐይቅ ላይ የእንቦጭ አረም መታየቱ ለጥናቱ አነሳሽ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የምርምር ሥራው የተለያዩ ደረጃዎች እንዳሉት የተናገሩት ዶ/ር ተሾመ የመጀመሪያው እርከን በዋናነት ምን ያህል የሚሆነው የሐይቆቹ ክፍል በአረሙ እንደተሸፈነ ማወቅ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን ለዚህም እንደ GIS እና የሳተላይት ፎቶ የመሳሰሉ ሳይንሳዊ ዘዴዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡ ይህም አረሙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

በምርምሩ ቀጣይ ደረጃዎች አረሙ በውኃው ባህሪ፣ በአስጋሪዎች፣ ውኃውን ለተለያየ ተግባር በሚጠቀሙ አካላት እና በሐይቆቹ ውስጥና ዙሪያ ባለው ብዝሃ-ሕይወት ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ በመለየት ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ምክረ ሐሳብ ይቀርባል፡፡

የምርምር ፕሮጀክቱ በሂደት እያደገ ሲመጣና ወደ መከላከልና ማስወገድ ሥራ ውስጥ ሲገባ ከፍተኛ ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችል የተናገሩት ዶ/ር ተሾመ ይህም በዩኒቨርሲቲው አቅም ብቻ ሊሠራ ስለማይችል ከውጪ አገራትና ተቋማት ጋር ለመሥራት ፕሮጀክቶች ይነደፋሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለምርምር ፕሮጀክቱ ውጤታማነት ያግዝ ዘንድ በአካባቢው ከሚገኙ ወላይታ ሶዶ፣ ዲላ እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የምክክር ሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንትና የምርምር ቡድኑ አባል ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው የእንቦጭ አረም በአገራችን የውኃ አካላት ላይ ከተከሰተ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን አስታውሰው በአሁኑ ጊዜ አረሙ በተለይ በሐይቆቻችን ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አያሳደረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አረሙ እያስከተለ ባለው ጉዳት ልክ ምርምሮች እየተደረጉ አለመሆናቸውንና በአብዛኛው እየተሠራ ያለው ሥራ የዘመቻ ሥራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ከጣና ሐይቅ ተሞክሮ በመውሰድ አረሙን በሰው ጉልበት ለመከላከል ጥረቶች ሲደረጉ የተስተዋለ ሲሆን ነግር ግን የሐይቆቹ ተፈጥሮ የተለያየ በመሆኑ ተሞክሮውን በቀጥታ በአባያ እና ጫሞ ሐይቆች ላይ መተግበሩ አደገኛ ሊሆን ስለሚችል ሥራዎቹ በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ መሆን እንዳለባቸው ዶ/ር ስምዖን አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡ በሐይቆቹ አካባቢ ባለው መሬት ላይ ያለውን አረም የመንቀል ሥራ ጉዳት እንደሌለው የተናገሩት ተመራማሪው በሁለትና በሦስት ዓመት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ሊታይ ባይችልም ዩኒቨርሲቲው ለውጡን ለማምጣት የምርምር ሥራውን በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

የአረሙን መስፋፋት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ስጋቱን ወደ ጥቅም የቀየሩ አገራት መኖራቸውና ይህንንም ወደ ተግባር ማምጣት የጥናቱ ሌላኛው ትኩረት መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ለጥናቱ ማስጀመሪያና ለመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ዩኒቨርሲቲው ከሦስት መቶ ሺ ብር በላይ መመደቡን ማወቅ ተችሏል፡፡